
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሟል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ተቋም የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ግንባታ እና የታዳሽ ኢነርጂ ልማት ላይ ሰፊ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ከ16ሺህ በላይ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የተበላሹ የውኃ ተቋማት ጥገና መከናወኑንም አንስተዋል። የውኃ አገልግሎት ብክነት ቅነሳን ከ22 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 21 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በክልሉ በሚገኙ ስድስት ከተሞች ላይ የሳኒቴሽን ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በኢነርጅ ዘርፍ ደግሞ ከ525 በላይ የባዮጋዝ ግንባታ መገንባት እንደተቻለ ገልጸዋል። ከ71ሺህ በላይ ሶላር እና ከ146ሺህ በላይ የተሻሻሉ ምድጃዎችን ማሠራጨት እንደተቻለም ተናግረዋል። በኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የውኃ ተቋማትን ወደ ፀሐይ ብርሃን (ሶላር) የመቀየር ሥራዎች ሲሠሩ መቆየቱን አንስተዋል። በዚህም ከ56 በላይ የውኃ ተቋማትን በፀሐይ ብርሃን እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾን ሥራ በግንባታ እና ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የጥገና ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የጥልቅ ጉድጓድ ጥናት፣ የውኃ መጠን ፍተሻ እና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ውስንነቶች የታዩባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። ከወረዳ እስከ ክልል ተቀናጅቶ በመሥራት እና ተግባራትን ቆጥሮ በመሥራት በዘጠኝ ወሩ ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ነው የጠቀሱት።
በውኃ እና ኢነርጅ ዘርፍ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያልተሠሩ ሥራዎች ስላሉ ከመንግሥት እና ከሕዝቡ ፍላጎት አንጻር ሥራዎች እየተለዩ በትኩረት ይሠራሉ ብለዋል። በዘጠኝ ወራት ውስንነት የታየባቸው ሥራዎችን በቀሪ ወራት ለማጠናቀቅ ሰፊ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የዞን ውኃ እና ኢነርጅ መምሪያ ኀላፊዎች ማኅበረሰቡን በውኃ እና ኢነርጅ ተግባራት ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰፊ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በዚህም መንግሥትን፣ ማኅበረሰቡን እና ረጅ ድርጅቶችን በማቀናጀት በተሠሩ ሥራዎች ጥሩ አፈጻጸም መመዝገቡን ነው የጠቀሱት። ነገር ግን በሁሉም ዞኖች እኩል አፈጻጸም እንደሌለ አንስተዋል።
የዛሬው የግምገማ መድረክ የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ዞኖች ተሞክሮ በመውሰድ በቀሪ ወራት ክፍተቶችን ለማስተካከል እና ተቀራራቢ አፈጻጸም እንዲኖር ለማድረግ ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
