
ደሴ: ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሒሳብ ባለሙያዎች ማኅበር ዓመታዊ የምርምር ኮንፈረንስ በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ብርሃን አስማሜ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው የሒሳብ ትምህርትን ተወዳጅ እና ተመራጭ በማድረግ ለዲጂታል ኢኮኖሚው የድርሻውን እንዲወጣ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል። በተለይም በክረምት ወራት ለተማሪዎች ልዩ ሥልጠና እና ድጋፍ እየሠጠ ነው ብለዋል።
በጉባኤው የሚቀርቡ ጥናቶችም የዘርፉን ክፍተት በመለየት መፍትሔ ለመፈለግ አጋዥ እንደሚኾኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሒሳብ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሳሙኤል አሰፋ (ዶ.ር) ሒሳብ ለሁሉም መሠረት በመኾኑ ማወቅ፣ መረዳት እና መተግበር፤ ለወቅታዊ እና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
የትምህርት ዘርፉን ተማሪዎች እንዲወዱት እና እንዲማሩት በጥናት እና ምርምር የታገዘ ተግባር እየተከናወነ መኾኑንም አብራርተዋል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሀገራዊ ምርምር እና ልማት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሀብታሙ አበራ (ዶ.ር) ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
በተለይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን እውን ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በመርሐ ግብሩ በሒሳብ ትምህርት ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረጉ 16 ዓለማቀፋዊ እና ሳይንሳዊ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ተብሏል።
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ 50 ተማሪዎች በሒሳብ ትምህርት ላይ የጥያቄ እና መልስ ውድድር በማካሄድ ለአሸናፊዎች ሽልማት ይበረከትላቸዋልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
