የዳኝነት አገልግሎትን ቀልጣፋ እና ዘመናዊ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሠርተዋል።

12
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እና በሥሩ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል። የተሠሩ ተግባራት ቀርበውም ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአይሲቲ ዳይሬክተር መኳንት አገኘሁ (ዶ.ር) ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ዲጂታል ለማድረግ ተሠርቷል ብለዋል።
የኔትወርክ፣ የደኅንነት ካሜራ እና በዘመናዊ መሳሪያዎች የታገዘ የዳኝነት ሥራ በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ መኾኑንም አንስተዋል።
ማንኛውም ባለ ጉዳይ ባለበት ቦታ ኾኖ መዝገብ እንዲከፍት የኢ ፋይሊንግ አገልግሎት ተጀምሯል ያሉት ዳይሬክተሩ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ክርክርን መከታተል እንዲቻል መሠራቱንም ጠቁመዋል።
ባለ ጉዳዮች በቤታቸው ኾነው በሞባይል መተግበሪያ አገልግሎት እንዲያገኙ ተሠርቷል ነው ያሉት። የአገልግሎቱ ዲጂታላይዝድ መኾን የባለ ጉዳዮችን ድካም እና ወጭ ቀንሷል፣ የሥራ ኀላፊዎች ባሉበት ቦታ ኾነው እንዲከታተሉ አድርጓል፣ የፍርድ አገልግሎት ጥራትን ጨምሯል ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስትራቴጅክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፍሬው ታደሰ በወረዳ እና በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በጥራት እና በቅልጥፍና አገልግሎት እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቶች ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን ተናግረዋል። በቀሪ ወራት መዛግብት እልባት እንዲያገኙ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። ጥራት ያለው መዝገብ እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በጥራት እና ቅልጥፍና አገልግሎትን የመስጠት ጠንካራ አፈጻጸም ታይቷል ብለዋል።
በዘጠኝ ወራቱ ዜጎች ባሉበት ቦታ ኾነው ፋይል ያስከፈቱበት፣ የአገልግሎት እርካታ የተፈጠረበት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የዳኝነት አገልግሎት የተሰጠበት እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች ላይ ዳኞችን በማሠልጠን ወደ ሥራ በመገባቱ ጥሩ ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል።
በቀሪ ወራት ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ይሠራል ነው ያሉት።
የዳኝነት አገልግሎትን ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ለማድረግ መሠራቱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ ዙር የዲጂታላይዜሽን ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ተምሳሌት የኾነ ፍርድ ቤት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባውን ባለ አራት ኮከብ ሆቴል አስመረቀ።
Next articleየሒሳብ ትምህርትን ተማሪዎች እንዲወዱት በምርምር የታገዘ ሥራ እየተሠራ ነው።