
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኃይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ግሩፕ በደብረ ብርሃን ከተማ በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የገነባውን ባለ አራት ኮከብ ሆቴል አስመርቋል።
በታሪካዊቷ የደብረ ብርሃን ከተማ የኃይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ግሩፕ 11ኛ መዳረሻውን ነው ዛሬ ያስመረቀው።
ሆቴሉ የከተማዋን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎም ይጠበቃል።
የኃይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ግሩፕ ባለቤት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ለሆቴሉ ግንባታ ከከተማ አሥተዳደሩ ለተደረገለት ቀልጣፋ እና ፈጣን አገልግሎት ምሥጋናውን አቅርቧል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ሆቴሉ ደብረ ብርሃን የቱሪዝም እና የዕውቀት ማዕከል እንድትኾን ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ይህ ግዙፍ ተቋም ከተማዋ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም እና የዕውቀት ማዕከል እንድትኾን በምታደርገው ጥረት ውስጥ የላቀ ሚና እንደሚጫወትም ተመላክቷል።
ሆቴሉ በሕንፃው ውበት ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሳቢ እና ምቹ አገልግሎት ለከተማዋ በማምጣቱ ትልቅ ዕድል መኾኑም ተገልጿል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ የ”ይቻላል” መንፈስን በተግባር ያሳየ የሀገር ኩራት መኾኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 50 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 370 ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል።
የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሆቴል መመረቅ በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የንግድ እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያነቃቃ ተስፋ ተጥሎበታል።
በምረቃው ላይ የተገኙት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና እንግዶች የሆቴሉን የሥራ አጀማመር እና ዘመናዊ አገልግሎቶች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ዮናስ ታደሰ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
