ሪፎርሙ የመንግሥት ሠራተኞችን ይቀንሳል?

33
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የአሠራር ሥርዓት ለማዘመን እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ነገር ግን ይህ ሪፎርም ሠራተኛን በሰበብ ከመንግሥት ሥራ ለመቀነስ ያለመ ነው የሚል ሃሳብ ይነሳበታል።
#እውነት ማሻሻያው ሠራተኞችን ይቀንሳል?
👉አሚኮ እውነታ ማጣሪያ አጣርቷል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሪፎርም ድጋፍ እና ክትትል ዳይሬክተር እንዳላማው ይታይህ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየተተገበረ ያለው አጠቃላይ የማሻሻያ ሥራ ዘርፈ ብዙ ዓላማዎች አሉት ይላሉ።
በዋናነኝነት የሠራተኛውን አቅም በመገንባት እና አሠራሮችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ ዋና ዓላማው ነው።
የሠራተኛውን የማስፈጸም አቅም፣ ዕውቀት፣ ክሕሎት እና የሙያ ሥነ ምግባር በማሳደግ ውጤታማ የሥራ ድባብ ለመፍጠርን ያለመ እንደኾነ አብራርተዋል።
ከሪፎርሙ ጋር ተያይዞ “በምዘና ሥም ሠራተኞችን ከሥራ ለመቀነስ ነው” የሚል አሉባልታ እየተነዛ መኾኑን ገልጸዋል ዳይሬክተሩ።
የሚደረገው ምዘና ዋነኛ አላማ ግን በሠራተኛው ዘንድ የሚታዩ የእውቀት፣ የክሕሎት ወይም የባሕርይ ክፍተቶችን መለየት ነው። ከተለዩ በኋላ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በሚዘጋጁ ሥልጠናዎች ሠራተኛውን አምራች እና ብቁ የማድረግ ሥራ ለመሥራት እንጅ ከሥራ ለማባረር አይደለም ነው ያሉት።
ከሪፎርሙ ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ወይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ እንደኾነም አብራርተዋል።
ይህ አሠራር አገልግሎቶችን ከወረቀት ንክኪ እና ከማኑዋል አሠራር በማላቀቅ ወደ ዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት የሚያሸጋግር እንደኾነ ነው ያስቀመጡት።
በዚህም ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ኾነው በቴክኖሎጂ አማካኝነት ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መኾኑ ተጠቁሟል።
አገልግሎት አሠጣጡ በቴክኖሎጂ መደገፍ ከሠራተኛው የአቅም ግንባታ ሥራ ጋር ተዳምሮ የሥራ ቅልጥፍናን እና ውጤታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
የማሻሻያ ሥራው ሲጠናቀቅ የሠራተኛው የሥራ ምርታማነት ያሳድጋል። የአገልግሎት ተደራሽነት እና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ የተገልጋዩ እርካታ ይጨምራል ነው ያሉት።
በአሉባልታዎች ከመወዛገብ ይልቅ በመንግሥት የተዘጋጁ የፖሊሲ ሰነዶችን እና መመሪያዎችን መመርመር እና ከተገቢ የመረጃ ምንጮች መረጃ መውሰድ እንደሚገባም መክረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል ከ896 በላይ አነስተኛ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
Next articleአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባውን ባለ አራት ኮከብ ሆቴል አስመረቀ።