
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብሪቲሽ አየር መንገድ በበረራ ላይ የዋይ-ፋይ አገልግሎትን በይፋ መጠቀም በመፍቀድ ቀዳሚው አየር መንገድ ኾኗል።
ዩኤስ ኤ ቱደይ በኤክስ ገጹ ዛሬ እንዳስነበበው አየር መንገዱ ይህን የፈቀደው በቅርቡ ባስተዋወቀው በሳተላይት የሚሠራ ከፍተኛ ፍጥነት ባለው የዋይ-ፋይ አገልግሎት አማካኝነት አገልግሎቱን ለመስጠት ነው።
አየር መንገዱም በይፋዊ የትስስር ገጹ እንደገለጸው ነጻ የስታርሊንክ ዋይ-ፋይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቅጃለሁ፣ ሰማይ ላይም ሆናችሁ ግንኙነታችሁ አይቋረጥም ብሏል።
አየር መንገዱ ይህን ቢፈቅድም በበረራ ወቅት የሚፈጠረውን ረብሻ ለመቀነስ የተለያዩ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉም አሳስቧል።
ማንኛውም የቪዲዮም ኾነ የድምጽ ጥሪ በጆሮ ማዳመጫ ብቻ ማድመጥ፤ ተሳፋሪዎች ሲያወሩ የሌሎችን ሰላም እንዳይነኩ ድምጻቸውን ዝቅ ማድረግ ይጠየቃሉ ብሏል። የበረራ አስተናጋጆች ሁኔታውን በቅርበት እንደሚከታተሉም ገልጿል።
ይህ አዲስ አሠራር በበረራ ወቅት ያለውን ጸጥታ ያጠፋዋል ወይስ የቴክኖሎጂ ዕድገት ውጤት ማሳያ የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
በሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
