
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ-ፈረንሳይ የቴክኖሎጅ ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ወጣት ዳግማዊ ዮሐንስ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው ተማሪዎች መማር የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጅ ፈጥሮ ሥራውን አስተዋውቋል።
ሥራው ከ4ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች በክፍል ደረጃቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው እንዲማሩ የሚያግዝ ነው።
ይስሃቅ አብርሃም ደግሞ ልጆች ጌም ተጠቅመው እንዲማሩ የሚያስችል ቴክኖሎጅ አስተዋውቋል።
ልጆች ከወላጆች ጋር በሞባይል አጠቃቀም የሚያጠፉትን ጊዜ ወደ ቁምነገር ቀይረነዋል ነው ያለው።
ፈጠራው ሕጻናት በሞባይል ጌም አማካኝነት ፊደል እና መሠረታዊ የሂሳብ ስሌቶችን በጨዋታ መልክ እንዲማሩ ያስችላቸዋል።
ዛሬ ላይ በወላጆች እና ሕጻናት መካከል በስልክ አጠቃቀም የሚታየውን ክፍተት ቁም ነገር እንዲማሩበት ወደሚያግዝ ስልት መቀየራቸውን የፈጠራ ባለቤቶቹ ተናግረዋል።
ሥራቸውም “እንጫዎት ጌምስ” በሚል ፕለይ ስቶር ላይ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
የአይስ አዲስ ኀላፊ ማህሌት ካሳየ በፎረሙ 24 ቴክኖሎጅ ላይ የሚሠሩ ስታርታፖች መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱንም አስታውሰዋል። ለስታርታፖች በሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት በመጡ ባለሙያዎች ሥልጠና መሠጠቱንም ገልጸዋል።
ለስታርታፖች ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ድጋፍ ተደርጓል። የፈረንሳይ ኤምባሲ የትብብር እና የባሕል ኀላፊ ላውረንት ሴራኖ የኢትዮ- ፈረሳይ የቴክኖሎጅ ፈጠራ ፎረም የቴክኖሎጅ ፈጠራን የሚያበረታታ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ተመሥገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
