ሕልመኛው ታዳጊ

12
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ገና በልጅነቱ በሰማይ የሚበሩ አውሮኘላኖችን ሲመለከት ትኩረቱን ይስቡት ነበር። ወላጆቹን ስለ አውሮኘላኖች አዘውትሮ ይጠይቅም እንደነበር ይናገራል። ከጥያቄ አልፎ ግን ያለውን ተሰጥኦ ከሰፈር የሚያገኛቸውን የወዳደቁ ዕቃዎችን በመጠቀም የፈጠራ ክህሎቱን “ሀ” ብሎ ጀመረ፤ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኤሮ ስፔስ ኢንጅነሪንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪው አማኑኤል መኳንንት።
በየቀኑ እየጠየቀ የሚያገኘውን ምላሽ ወደ ተግባር በመለወጥ በካርቶን አውሮፕላን አስመስሎ በመሥራት ሕልሙን ዕውን የማድረግ ሥራውን ጀምሯል። ከዚያም የባትሪ ድንጋይ በመጠቀም የሚንቀሳቀስ መኪና የሚመስል ትንሽ ሞዴል ፈጠራ መሥራቱን ነግሮናል።
እያደገ ሲመጣ ከትምህርቱ ጎን ለጎን መረጃዎችን ከዩቲዩብ በመሠብሠብ ክህሎቱን ማሳደጉን ገልጾልናል። ፈጠራውንም አስቀጥሏል።
በወቅቱ ግን የፈጠራ ሥራውን መስሪያ ቁሳቁስ ለመግዛት ገንዘብ እንዳልነበረው አውስቷል። ከዚያም በትርፍ ሰዓቱ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ጥገና ሥራዎችን በመሥራት ገንዘብ ማግኘቱን የሚናገረው ተማሪ አማኑኤል ባገኘው ገንዘብ መስሪያ ቁሳቁስ በመግዛት በሪሞት የሚንቀሳቀስ አውሮፕላን የፈጠራ ውጤትን ዕውን አድርጓል።
ከብዙ ጥረት በኋላ አኹን ላይ የልጅነት ሕልሙ እያደገ በሪሞት የሚንቀሳቀሱ ሰው አልባ አውሮኘላኖችን እየሠራ የፈጠራ ሥራውን እያሳደገ ይገኛል።
በፈጠራ ሥራውም ከተለያዩ ተቋማት ዕውቅና ማግኘቱን ገልጿል። ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በሚያደርግለት እገዛም የተሻሉ የፈጠራ ሥራዎች እየሠራ መኾኑን ተናግሯል። የወላጆቹ ድጋፍ ከፍተኛ መኾኑን የሚገልጸው ተማሪ አማኑኤል “አኹንም የማሳካው ሕልም አለኝ” ይላል።
ለወደፊትም የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች ለማበረታታት፤ በግብርናው ዘርፍ ለኬሚካል ርጭት የሚያገለግሉ በሪሞት የሚንቀሳቀሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመሥራት ወደ ገበያ ለማቅረብ አልሟል። ይህ ደግሞ የአርሶ አደሮች ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትን ለመቆጠብ እና ጤንነቱን ለመጠበቅ ድርሻው የጎላ እንደሚኾን ነው የተናገረው።
ለአብነት ተማሪ አማኑኤልን አነሳን እንጂ በተለያዪ ዘርፎች በርካታ ሕልም ያላቸው ታዳጊዎች አሉ። እነዚህ ታዳጊዎች የሀገሪቱን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዕውን ለማድረግ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። እንደነዚህ አይነት የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ማድረግ እንደሚገባም ተማሪ አማኑኤል ተናግሯል።
የፈጠራ ሥራዎች የማኅበረሰቡን ችግር ቀላል እንዲያደርጉ የሚመለከተው አካል የሚያደርገውን ክትትል እና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቋል።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየባሕር በር ጥያቄ ከታሪካዊ መብት እስከ ዓለም አቀፍ የሕግ ድጋፍ
Next articleየኢትዮ -ፈረንሳይ የቴክኖሎጅ ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄደ።