
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በታሪክ በተፈጠረ እጥፋት ኢትዮጵያ ከባሕር በር ባለቤትነት እና ተጠቃሚነት ርቃ ቆይታለች። አሁን ደግሞ የባሕር በር ባለቤት ለመኾን ጥያቄ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
በሕዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ የሚያንሱ ሀገራት የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግን መሠረት በማድረግ የባሕር በር ተጠቃሚ ኾነዋል።
ለአብነት ሲውዘርላንድ የኔዘርላንድን፤ ቦልቪያ የችሊን ወደቦችን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተፈቅዶላቸው የባሕር በር ባለቤት በመኾን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ከላይ የተጠቀሱ ሀገራት የራሳቸው ባሕር ባይኖራቸውም ከጎረቤት ሀገራት የባሕር በር ባለቤት በመኾን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ ኾነዋል።
ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ የባሕር በር የወጣቶች አምባሳደር እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መሐመድ መሐሙድ ኢትዮጵያ ለዘመናት የወደብ ባለቤት እንደነበረች አስታውሰዋል።
በታሪክ በተፈጠረ እጥፋት የባሕር በሯን ማጣቷን ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የግዛት መስፋፋት ሳይኾን የተጠቃሚነት ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር በር እንዲያገኙ በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ከአንቀጽ 124 እስከ 133 ያሉ ሕጎች እንደሚደነግጉ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ ካላገኘ በአፍሪካ ኅብረት የጸጥታ ምክር ቤት እና በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት የባሕር በር ጥያቄዎን ማስመለስ እንደምትችል ጠቁመዋል።
ጥያቄው በውይይት እና በድርድር እንዲፈታ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሠራች መኾኗንም አንስተዋል።
የፖለቲካ ልዩነትን በማስቀረት የባሕር በር ጥያቄው የሉዓላዊነት እና የተጠቃሚነት ጉዳይ መኾኑን መረዳት እንደሚገባ ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በቁርጠኝነት ድጋፍ እንዲያደርግም አስገንዝበዋል።
መንግሥት የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ጥያቄ ኢትዮጵያ ማቅረቧን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለጎረቤት ሀገራት እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ማስረጽ እንዳለበትም መክረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
