ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ሳይንስ ምርምር በርካታ ሥራዎችን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሠርቷል።

8
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል።
አምባሰደሩ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ ( ዶ.ር) እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው መሪዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ጉብኝቱ እና ውይይቱ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካ ኤምባሲ እና በአሜሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሠራቸው ያላቸውን ሥራዎች ለማጠናከር ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በጋራ የተሠሩ ሥራዎችን ዕውቅና በመስጠት እና ወደፊትም ሥራዎችን አጠናክረን ለመቀጠል ሰፊ ውይይት አድርገናል ነው ያሉት።
ውይይቱ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሜሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እንደሚያስችለው አንስተዋል።
አምባሳደሩ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን ጉዞ ለማጠናከር እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል። በአማራ ክልል ያለውን የትምህርት ችግር ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው እየሄደባቸው የሚገኙ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን መደገፍ በሚያስችል ሁኔታ ላይ መምከራቸውንም አንስተዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራውን ሥራ ኤምባሲው ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በብቸኝነት ያለው የልህቀት ማዕከል መኾኑን ነው ያነሱት።
ለምርምር የሚያገለግሉ ዘመናዊ ቤተ ሙከራዎችንም ጎብኝተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ በምርምር ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሊያስተሳስር የሚችል መኾኑን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የምርምር ሥራዎችን በጋራ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት። ወጣት የፈጠራ ባለተሰጥኦዎች በአሜሪካ ሀገር የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሪ ቀርቦልናልም ነው ያሉት። ኤምባሲው ለሰጣቸው ዕድልም ምሥጋና አቅርበዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካ ኤምባሲ እና ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚሠራው ሥራ ሰፊ መኾኑንም ተናግረዋል። የአሜሪካ ኤምባሲ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የራስገዝነት ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የገለጹት።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመኾን የሚያስችለው አቅም ያለው ትልቅ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ሳይንስ ምርምር በርካታ ሥራዎችን የሠራው ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመኾን ነው ብለዋል። የዛሬው ውይይት እና ጉብኝት እስካሁን የነበሩ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያስችላል፤ ዩኒቨርሲቲውም የትብብር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleበተሠበሠበው ገቢ ለትውልድ የሚተርፉ ልማቶች ተሠርተዋል።
Next articleየባሕር በር ጥያቄ ከታሪካዊ መብት እስከ ዓለም አቀፍ የሕግ ድጋፍ