
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች እና መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እየተሠሩ ያሉትን የልማት ሥራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሻለ ገቢ በመሠብሠብ 69 በመቶ መፈጸም መቻሉን ገልጸዋል።
ክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ በሠበሠበው ገቢ በከተማዋ ለትውልድ የሚተርፉ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
ከተማ አሥተዳደሩ ከዕቅድ በላይ ገቢ በመሠብሠብ በከተማዋ የበለጠ ልማት እንዲሠራ ቢሮውም የድጋፍ ቡድን መድቦ እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጉብኝቱ ገቢ ተሠብሥቦ የልማት ሥራዎች ላይ የሚውል መኾኑን የገቢ ሠብሣቢ ባለሙያዎች በተግባር እንዲያዩት ለማስቻል ያለመ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማዋ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከሕዝብ የሚሠበሠበውን ገቢ በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል ባሕር ዳርን ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ እንድትኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች አማካሪ አግማስ ጫኔ እንዳሉት ሕዝብን ያማከለ፣ ልማትን የሚያፋጥን እና የተሻለ ገቢ በመሠብሠብ በኩል በየዓመቱ እየተሻሻለ መጥቷል።
የሚሠበሥቡት ገቢ ልማት ላይ ውሎ የሥራቸውን ውጤት በማየታቸው እንደተደሰቱም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
