በአማራ ክልል ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሠራ ነው።

6
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ በሰሜን ወሎ ዞን የመቄት ወረዳ ሐና መኳት ቀበሌ ነዋሪዎች ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።
በቀበሌው የገጠር ከተማ በሚገኝ አንድ አነስተኛ የውኃ ቧንቧ ላይ ለመድረስ አምስት ኪሎ ሜትር ተጉዘው፣ ገንዘብ ከፍለው እና ውኃውን በእንስሳት ጀርባ ጭምር እያጓጓዙ እንደሚጠቀሙ ነግረውናል። ገንዘብ እና ጉልበት የሌላቸው አቅመ ደካሞች ውኃ ማግኘት አይችሉም ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት በቀበሌው የተጀመረውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንዲያጠናቅቅላቸውም ጠይቀዋል።
የሐና መኳት ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት አማካሪ ዮሴፍ አድኖ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቱ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ የኾነ በጀት ተይዞለት ወደ ተግባር ተገብቶ እንደነበርም ነው የገለጹት። ከ9 ሺህ 200 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የሚታሰብ ፕሮጀክት ነው። ግንባታው አሁን ላይ 86 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል ብለዋል አማካሪው።
ይሁንና በጸጥታ እና በተቋራጭ አቅም ችግር ተቋርጦ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ውኃ እና ኢነርጅ መምሪያ ኀላፊ ፋሲል አረጋ የዞኑ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት በገጠር 65 ነጥብ 2 በመቶ፤ በከተማ ደግሞ 67 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።
🚰 የዞኑ የውኃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል እና በክልሉ መንግሥት ከተጀመሩ 11 የውኃ ተቋማት መካከል ሰባቱ በዚህ ዓመት ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አንድ በፌዴራል እና ሦሥት በክልሉ መንግሥት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በግጭት ወድመው እና ተቋርጠው እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ኀላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። የገጠሩን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ከ76 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 79 በመቶ እና የከተማውን ደግሞ ከ78 ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል ነው ያሉት።
🚰 የበጀት ዓመቱ የገጠር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ፦
👉 2 ሺህ 445 አነስተኛ የውኃ ተቋማትን ለመገንባት እቅድ ተይዟል።
👉 ከዚህ ውስጥ በ8 ወሩ 603 ግንባታቸው ተጠናቅቋል ብለዋል።
👉 ከ1 ሺህ 900 በላይ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
👉 ከ50 በላይ መካከለኛ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በክልሉ መንግሥት እና በዓለም ባንክ ድጋፍ ተጀምረው 13ቱ መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል።
👉 የንጹሕ መጠጥ ውኃ ሽፋኑ ከነበረበት በ1 ነጥብ 3 በመቶ ጨምሯል ነው ያሉት።
🚰 የበጀት ዓመቱ የከተሞች የውኃ ፕሮጀክት ግንባታ፦
👉 30 መካከለኛ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል።
👉 ባለፉት ስምንት ወራት ስምንት የውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል።
👉 የንጹሕ መጠጥ ወኃ ሽፋኑ ከ1 ነጥብ 5 በመቶ በላይ አድጓል ብለዋል ኀላፊው።
የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የተቋረጡ ፕሮጀክቶች እንድጠናቀቁም ጥረት እየተደረገ እንደኾነ አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleግጭት ተወግዶ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል።
Next articleበተሠበሠበው ገቢ ለትውልድ የሚተርፉ ልማቶች ተሠርተዋል።