ግጭት ተወግዶ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል።

6

 

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር “እኔ በሰውነቴ ከማንም አልበልጥም፣ አላንስም! እርስዎስ?” በሚል መሪ መልዕክት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የተገኙት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) የሰው ልጅ ክብር የሚጠበቅባት፣ ግጭት የሚወገድባት እና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር ኤርጎጌ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ፣ ሴቶችን ከጥቃት ለመጠበቅ፣ የአካል ጉዳተኞች መገለል እንዳይኖር፣ የሕጻናትን መብት ለማስከበር እና ለአረጋውያን ተገቢውን ክብር ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ሕጎች እና ፖሊሲዎች ተቀርጸው እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአካል እና በአስተሳሰብ የሚደርሱ ጥቃቶች እየታዩ መኾኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ለእነዚህ ጥቃቶች ዋነኛው መነሻ በሰዎች ልቦና ውስጥ ያለው የተዛባ አመለካከት መኾኑን አስረድተዋል።

ሀገሪቱ ለሌሎች አርዓያ የሚኾኑ ጠንካራ ህጎች ቢኖሯትም ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር እንዳይቀየሩ እንቅፋት የሆነው “የልቦና ውቅር መዛባት” መኾኑን ገልጸዋል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውሥብሥብ ችግሮች አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት የሰው ልጅ ለሰው ልጅ ያለው ክብር መሸርሸር መኾኑን ለማስገንዘብ እንደኾነ ተገልጿል።

የሃይማኖት ተቋማት ከመንፈሳዊ መመሪያነታቸው ባለፈ ለማኅበራዊ ትስስር ዋልታ እና ማገር መኾናቸውን ጠቁመዋል። ዶክተር ኤርጎጌ ቢከናወኑ ያሏቸውን ተግባራት ጠቅሰው እንዳሉት አድሎና መገለልን ከመሰረቱ መናድ ይገባል።

የግጭት መነሻ የኾነውን የልዩነት አመለካከት ማረምም ተገቢ እንደኾነ ጠቁመዋል። አማኙን በማስተማር ረገድ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የመምረጥ እና የመመረጥ መብትን መጠቀም ከኢትዮጵያዊ ሁሉ ይጠበቃል” የሃይማኖት አባቶች
Next articleበአማራ ክልል ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሠራ ነው።