መገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር በኩል ሊሠሩ ይገባል።

4

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን “መገናኛ ብዙኀን ለሀገር ግንባታ እና ለማኅበረሰብ አመለካከት ቀረጻ” በሚል መሪ መልዕክት ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በመድረኩ ላይ ባለፉት ሦሥት ወራት በሕዝብ እና በማኅበረሰብ የመገናኛ ብዙኀን የተከናወኑ የይዘት ሥራዎች ተገምግመው የጥናት ውጤት ቀርቧል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ እንደገለጹት፤ የመገናኛ ብዙኀን አዋጁ ከተሻሻለ በኋላ ተቋማቱ በማኅበረሰብ አቀፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ባለፉት ሦሥት ወራት ከሕዝብ፣ ከሃይማኖት ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ መኾናቸውን ጠቁመው የዛሬው መድረክ ደግሞ ከመገናኛ ብዙኀን መሪዎች ጋር በጋራ የአዝማሚያ ትንተና ግኝት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር፣ የወል ትርክትን በማስረጽ እና ለጋራ ዓላማ በቅንጅት በመሥራት ረገድ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኀንን ከመቆጣጠር ባለፈ ሥራቸውን በነጻነት እና ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲሠሩ እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሚዲያዎች ብዝኀነትን ታሳቢ ያደረጉ፣ አንድነትን የሚያጎሉ እና ሀገርን ወደ ከፍታ የሚያወጡ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የማኅበረሰቡን ቋንቋ፣ ባሕል እና እሴት በማሳደግ ረገድ የሚዲያ ተቋማት ሚና ቁልፍ መኾኑንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ሦሥት ወራት በይዘት ትንተና ጥናት ካካሄደባቸው ተቋማት መካከል10 የሕዝብ ሬዲዮ እና 12 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ 32 የማኅበረሰብ ሬዲዮ እና 6 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይገኙበታል።

በእነዚህ ተቋማት ላይ የተደረገው የይዘት ትንተና የታዩ ጠንካራ ጎኖችን እና ክፍተቶችን የለየ ሲኾን በአሁኑ ወቅት የክልል የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ተወካዮች፣ የማኅበረሰብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ኀላፊዎች በተገኙበት በጥናቱ ውጤት ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። ተሳታፊዎቹም ሀገርን የሚያሳድጉ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በይበልጥ ለመሥራት መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ዘጋቢ ፦ ሐናማርያም መሥፍን

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የአገልግሎት ቅልጥፍናን እና ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleዛሬ ሥራ የጀመረው የመሶብ ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት በውስጡ ምን ይዟል ?