
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሀገራዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ የኾነ የባሕል ለውጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ካቀድናቸው አምስት የልማት ምሰሶዎች መካከል ቴክኖሎጂን ለአገልግሎት ዘርፉ እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናን እና ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት።
መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የጀመርነው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም በመሶብ አገልግሎቶች የታየው ከፍተኛ የደንበኞች እርካታ የዚህን የሥራ ሞዴል ውጤታማነት በግልጽ አረጋግጧል ብለዋል።
ይህም አሠራሩን ይበልጥ ማስፋፋት አስፈላጊ መኾኑን ያመላክታል። ዛሬ በይፋ የተመረቀው የመሶብ የሞባይል አገልግሎትም የዚሁ ቀጣይነት ያለው የሥራ እንቅስቃሴ አካል መኾኑን ገልጸዋል።
ዜጎቻችን ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ትርጉም ያለው የጊዜ ቁጠባ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ እነዚህን የተቀናጁ አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ሥራችንን የምንቀጥል ይኾናል ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
