
ደሴ: ሚያዚያ 13/2018 (አሚኮ) “2ኛ ዙር ቀበሌ የመድረስ ምዕራፍ” የተሰኘው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ሪፎርም ንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተጀምሯል። ለስምንት ቀናት የሚቆየው ይህ መድረክ ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያሳተፈ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናን ያካተተ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በስድስት የምልመላ ማዕከላት ከ4 ሺህ በላይ ሠልጣኞች እየተሳተፉ ነው። የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት የሪፎርም ዓመታት በካፒታል መጠን ዕድገት፣ በቁጠባ ባሕል እና ውዝፍ ገንዘብን በማስመለስ ረገድ ተስፋ ሰጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።
የአፋር ክልል የማኅበራት ማደራጀት እና ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አብዱ ሀሠን በበኩላቸው፣ በክልሉ የለውጥ ሥራው በቅርቡ ቢጀመርም ዘመናዊ አሠራርን በመተግበር ረገድ ውጤቶች እየታዩ መኾኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በመክፈቻው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሥልጠናው በዘርፉ የሚስተዋሉ የፈጻሚዎችን የአቅም ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። የለውጥ ሥራዎች በተግባር የሚፈተሹ መኾናቸውን ያመለከቱት ዋና አፈ ጉባኤዋ የመንግሥት፣ የባለሀብቱ እና የማኅበረሰቡ ቅንጅት ለስኬቱ ወሳኝ መኾኑን አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አምባዬ ወልዴ ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ89 ሺህ በላይ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ይገኛሉ። ባለፉት ሁለት ዓመታት የመረጃ ጥራትን በማረጋገጥ፣ ማኅበራትን መልሶ በማደራጀት እና ተቋማቱን በተማረ የሰው ኀይል እንዲመሩ በማድረግ አመርቂ ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል።
ይህ ለስምንት ቀናት የሚቆየው ሥልጠና በስድስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰጥ ታውቋል።
ዘጋቢ፦ ሕይወት አስማማው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
