
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት ለውጠዋል። ማኅበራዊ ሥርዓትን የበለጠ ለማስተሳሰር የሚኖራቸው ፋይዳም ጉልህ ነው።
በአንጻሩ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ አለመጠቀም መልካም እሴቶች እንዲሸረሸሩ፣ አሉታዊ ተጽዕኖዎች እንዲሰፉ ያደርጋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮምኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ዳይሬክተር ውቤ በላይ ማኅበራዊ ሚዲያ መረጃን በፍጥነትና በጥራት ለመድረስ ዘመናዊ የኢንተርኔት ሥርዓት የሚጠቀም መኾኑን ገልጸዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ “ለምንጋራቸው እና ለምናጋራቸው” መረጃዎች ትክክለኛነት ኀላፊነት መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ተጠቃሚዎች ሀሰተኛ ገጾችን እና መረጃዎችን ለመለየት የሚያስችል ግንዛቤ ማዳበር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
ደጋግሞ ማረጋገጥ፣ የልጥፍ ጊዜያቸውን ማስተዋል፣ በጥድፊያ እና በተጽዕኖ ውሳኔ አለመወሰን ተገቢ መኾኑን አንስተዋል።
ሌላኛው ሃሳባቸውን ያጋሩን በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ትምህርት ክፍል መምህሩ ኤልያስ ገብሩ ልክ ያልኾነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የእረፍት እና የሥራ ሥርዓትን በማዛባት ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ የተደረጉ ጥናቶች አሳይተዋል ብለዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ለዕይታ ታስበው የሚዘጋጁ የባህር ማዶ የአኗኗር ሥርዓቶችን በመመልከት ወጣቶች ተስፋ የመቁረጥ የሥነ ልቦና ጫና እየተፈጠረባቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ከነዚህ እና መሰል ችግሮች ለመውጣት ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ መቀነስ፣ ስለሚጠቀሙት የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘትና መልዕክት በቂ ግንዛቤ መውሰድ እንደሚገባቸውም መክረዋል።
ልክ ያልኾነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ወደ ሱስነት የማደጉ እድል ከፍተኛ ነውም ብለዋል። በመኾኑ በጊዜ የመፍትሔ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በደረጀ ደርበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
