
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት አገልግሎትን በማዘመን የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ ታስቦ ተግባራዊ የተደረገው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአማራ ክልል ገና ከጅምሩ አዲስ ተስፋን ይዞ መጥቷል።
በባሕር ዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ተገልጋዮችም ያለምንም መጉላላት በአጭር ጊዜ እየተስተናገዱ መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል።
ወይዘሮ አፍራም መሐመድ በማዕከሉ የስመ ንብረት አገልግሎት ለማግኘት ሄደው በማይታመን ፍጥነት ባገኙት አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸውልናል። አስተናጋጆችም በፈገግታ ተቀብለው እኛም ተደስተን ጉዳያችን እየተፈጸመልን ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።
ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ደሴ ገብረእግዚአብሄር በፊት የተንዛዛ የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ አሁን ላይ በማዕከሉ በተቀላጠፈ መንገድ መሥጠት መጀመሩ የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ጤናው ምህረት በ12 ተቋማት የሚሰጡ 73 የአገልግሎት ዓይነቶችን በአንድ ማዕከሉ እየተሰጡ ነው ብለዋል። ከ26 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎችም አገልግሎቱ ተደራሽ ኾኗል ነው ያሉት።
የተገልጋዮችን እርካታም 97 ነጥብ 6 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል። በቀጣይም ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎትን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን አመላክተዋል።
የመንግሥት አገልግሎትን በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በስፋት እየተሠራበት መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንችአምላክ ገብረ ማርያም ናቸው።
በባሕር ዳር እና ደሴ ከተሞች ባሉት ሦስት ማዕከላት ከ75 ሺህ በላይ አገልግሎቶችን መሥጠት እንደተቻለም ተናግረዋል። እስካሁን ባለው አፈጻጸምም የተገልጋይ እርካታ ከ97 በመቶ በላይ መድረሱን ነው የተናገሩት።
በቀጣይም በስድስት ሪጆፖሊታንት ከተሞች እና በ25 መካከለኛ ከተሞች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
#አሚኮ #መሶብ #ባሕር-ዳር #አማራ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
