
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 13/2018 (አሚኮ) የአፍሪካን የማይበገር የአየር ንብረት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚቲዮሮሎጂ ማኅበረሰብን ማዘመን በሚል መሪ መልዕክት ለሦሥት ቀን የሚቆይ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የዓለም ሚቲዮሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና 1 ተወካይ ፈጠነ ተሾመ ጉባኤው የሚቲዮሮሎጂ ሳይንስን ለማሳደግ እንዲሁም በሀገራት እና በአጠቃላይ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር ለተጀመረው የጋራ ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ሁሉም እዚህ የተገኘው የተለያዩ ሀገራትን፣ ድርጅቶችን፣ የሙያ ዘርፎችን እና ልምዶችን በመወከል እንደኾነ አብራርተዋል። አቶ ፈጠነ የእኛ አንድነት ለአህጉራችን፣ ለፕላኔታችን እና ለወደፊት ትውልዱ ጥቅም ሲባል አዳዲስ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማግኘት ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የተገኙት የአፍሪካ የሚቲዮሮሎጂ ማኅበረሰብ ቦርድ ሊቀመንበር ቡሩሃኒ ንየንዚ (ዶ.ር) ወጣት ተመራማሪዎች በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፉ ማበረታታት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለትንበያ ሥራዎች መጠቀም የአህጉሪቱን የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል ብለዋል።
በጉባኤው ዕውቀትን መጋራት፣ ትብብርን ማጠናከር፣ ሙያዊ ዕድገት እና የልምድ ልውውጥ ይደረግበታም ብለዋል።
የዓለም የሜትዮሮሎጅ ድርጅት የአሀጉሪቱን የሜትዮሮሎጅ ማኅበረሰብ ለማገዝ ቁርጠኛ መኾኑም በዚሁ መድረክ ተመላክቷል::
በአፍሪካ ሜትዮሮሎጅ ማኅበረሰብ ሳይንሳዊ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ታድመውበታል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
