
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የሀገር በቀል ዕውቀቶች ለዘመናዊ ሥልጣኔ ያላቸው ፋይዳ” በሚል እሳቤ በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
በአያልነህ ሙላቱ የሥነ-ጥበብ በጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት የተዘጋጀው ውይይቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጋዥነት በኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ነው የተካሄደው።
የድርጅቱ መሥራች ደራሲ እና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ “ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለችግሮቻችን መፍትሔ፤ ለሀገራችን ዕድገት እና ሥልጣኔ መሠረት ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
ዘመናዊ ትምህርት ከ100 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል ያሉት ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት የሕንጻ ግንባታችን ምን ያህል እኛን ይመስላል?፣ ምን ያህልስ እርሻችንን ከበሬ ቀንበር እና ሞፈር አውጥተናል ብለን መጠየቅ አለብን ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዮሐንስ አድገህ (ዶ.ር) ሀገር በቀል ዕውቀት ለሁላችንም ሊያሳስበን እና ሊያነጋግረን የሚገባ ነው ብለዋል።
እንደ ትምህርት ሚኒስትር ከ50 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሀገር በቀል ዕውቀት ዴስክ መቋቋሙን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም የሀገር በቀል ምርምር ማዕከል መቋቋሙን ተናግረዋል።
በውይይቱ ሀገር በቀል ዕውቀት ኢትዮጵያዊ ፊደል፣ ጽሑፍ እና ንባብ፣ ባሕላዊ የእርቅ እና የግጭት አፈታት ሥርዓት፣ እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀት እና ባሕላዊ ሕክምና በኢትዮጵያ የሚሉ ሦሥት ጥናታዊ ጽሑፎች ለውይይት ቀርበዋል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
