
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 13/2018 (አሚኮ) ሦሥተኛው ዓመታዊ የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምር ጉባኤ እተካሄደ ነው።
“የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምር በዲጂታል ዘመን” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ዓለምአቀፍ የቅርስ ተመራማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የቅርስ ሥብሥቦችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዞ መመዝገብ እና ማሥተዳደር የሚያስችለውን ሥራ በአጭር ጊዜ እና በረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
በተለይም ከኢትዮጵያ ዲጂታል 2030 ጋር የተናበቡ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዘርፉን በዲጂታል መልኩ ማዘመን የግድ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ይህንን ለማሳካትም ጉባኤው ቁልፍ መኾኑንም አስረድተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ እንደገና አበበ (ዶ.ር) በበኩላቸው በጥንታዊ ሥልጣኔ በባሕል እና በቅርስ ሀብታም የኾነችው ኢትዮጵያ ካለፉት ጊዜያት በተሻለ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ለማስተዋወቅ ሚኒስቴሩ ከቅርስ ባለሥልጣን እና ከዓለማቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ዘላቂነት ያለው ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው በቅርስ ጥበቃ እና ልማት ዘርፍ አዳዲስ እቅዶችን በማስተዋወቅ፣ ወቅታዊ ተግዳሮቶችን በጥናት እና ምርምር የመፍታት፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚኾኑ ሀሳቦች ተንፀባርቀው ዘርፉ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዲጂታል አሠራር እንዲተገብር አቅጣጫ የሚያመላክት ይኾናልም ተብሏል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲኾን ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ሁለት ጉባኤዎች የቀረቡ የምርምር ውጤቶች የታተሙበት መጽሐፍም በመድረኩ ይፋ ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
