
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 12/2018 (አሚኮ) የኢሜግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ በመደበኛ እና አስቸኳይ ፓስፖርት፣ በቪዛ፣ በትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ እና ሌሎች የይለፍ እና የጉዞ ሰነዶችን ለደንበኞች በመስጠት እንዲሁም በአየር እና የብስ ድንበር ቁጥጥር እና ሌሎች የተቋሙ አገልግሎቶች ባለፋት ዘጠኝ ወራት ስኬታማ ሥራዎች መሥራቱን ተናግረዋል።
ባለፋት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት እና 824 ሺህ 951 የቪዛ አገልግሎት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ለ29 ሺህ ሰዎች የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ በመስጠትም የተሳካ የዕቅድ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል። የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት በአየር እና በየብስ ድንበር ዓለማቀፍ ስታንዳርዶችን በጠበቀ መልኩ በጉዞ ሰነድ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ገቢ እና ወጭ መንገደኞች አገልግሎት ስለመስጠቱም ጠቁመዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በሕገ ወጥ መንገድ የኦላይን የአስቸኳይ ፓስፖርት የሚሞሉ፣ የድለላ ተግባር ውስጥ የተሳተፉ እና የተቋሙን ስም በአሉታዊ መንገድ እንዲነሳ ያደረጉ አካላት ላይ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በጋራ በመተባበር በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በ23 ቅርንጫፎች የተቀላጠፈ እና ተደራሽነቱ የሰፋ የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
ተቋሙ የነበረውን አሮጌ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በማቆም ወደ አዲስ የዲጂታል ሲስተም በመሻገሩ ትልቅ አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ከሀገር ውስጥ አገልግሎት እና በቆንስላ ከሚሰጡ አገልግሎቶች በድምሩ 30 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መሠብሠቡንም ተናግረዋል።
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ለኅብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጫው ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
