ኢትዮጵያ ያደረገችው የኢኮኖሚ ሪፎርም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አንዲያድግ አድርጓል።

4
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 12/2018 (አሚኮ) የኢትዮ-አውሮፓ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
“የዓለም አቀፍ አቅሞችን መክፈት” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄደው ፎረሙ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲኬላ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት የኢንቨስትመንት አማራጭ ዕድል የመክፈት አቅም ያላት ሀገር እንደኾነች ተናግረዋል።
አውሮፓ እና ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ የቆየ ትብብር ያላቸው መኾናቸውን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ለዲጂታል ሪፎርም የሰጠችው ትኩረት የሚበረታታ ነው ብለዋል። በቀጣይም የ140 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬላ ሜኔ እ.አ.አ በ2024 ብቻ በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል የ220 ቢሊዮን የንግድ ልውውጥ ተከናውኗል ብለዋል።
የጂኦ ፖለቲካ አለመረጋጋት እና የኢኮኖሚ መረጋጋት በሌለበት ጊዜ ትብብር ወሳኝ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ያደረገችው የኢኮኖሚ ሪፎርም በእርግጠኝነት ትብብሩን ከዚህ ወደ ተሻለ ሁኔታ ያሸጋግረዋል፤ እሰከ አሁን ይህ ማሻሻያ የቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ስኬታማ ነበር ብለዋል። በተለይ በፋይናንስ በዲጂታላይዜሽን፣ በቴክኖሎጅ እና በአሠራር የተደረጉ ሪፎርሞች ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥረዋል ነው ያሉት።
የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታ ሳማሪታ ሰዋሰው ይህ ፎረም በዲጂታል እና በኀይል ግንባታ ዘርፍ እገዛ የነበረውን የኅብረቱን ሥራ አጠናክሮ ያስቀጥላል ብለዋል።
በፋይናንስ፣ በቴሌ፣ በቴክኖሎጂ፣ በባንክ፣ በፋይናንስ፣ በዲጂታላይዜሽን የተሠሩ ሪፎርሞች ትልቅ ለውጥ እያመጡ እና የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ አንደኾነም አመላክተዋል።
ሕግ እና መመሪያዎችን በማሻሻል በአልሚዎች ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሁነቶችን አሻሽለናል፤ የታክስ ማነቃቂያ እና መደጎሚያ መመሪያዎችም ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በፎረሙ የአውሮፓ-ኢትዮጵያ የዲጁታል ኢኮኖሚ ፓኬጅ ሰምምነትም ተፈርሟል። ኢትዮጵያ ለወሰደችው የኦኮኖሚ እና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ እገዛ የሚያደርግ ሰምምነት እና የአፍሪካ ነጻ ገበያ ትብብርም ተፈርሟል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleልማትን የሚያፋጥንን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰድ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
Next articleየመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የማጥራት እና በዲጂታል የማደራጀት ሥራ ወሳኝ ነው።