
ደሴ: ሚያዚያ 12/2018 (አሚኮ) የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የመረጃ ማረጋገጥ ሥራ ለማከናወን ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የደሴ ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ኡስማን ሙሐመድ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ማረጋገጫ ሥራ ከግንቦት ወር ጀምሮ ለሦሥት ወራት ያክል እንደሚከናወን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በዚህ ሥራ ለሚሳተፉ የመስክ ሠራተኞች ሥልጠና እየሰጠ መኾኑን አንስተዋል። ይህ አሠራር በተለያዩ መደቦች ላይ ኾነው ከአንድ በላይ ክፍያ የሚያገኙ አካላትን መረጃ በማጥራት ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን እውን ለማድረግ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ተደራጅቶ መያዝ እንዳለበት ጠቅሰዋል። ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ መኾኑንም አመላክተዋል።
ባለድርሻ አካላትም በቀጣይ በሚከናወኑ መረጃ የማጣራት ሥራዎች እገዛ ለማድረግ ዝግጁ እንዲኾኑ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ካሳ አበባው እንደ ሀገር የተጀመረውን አዲሱን የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ መሠረት በማድረግ የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ በሥርዓት መያዝ ይገባል ብለዋል።
በዚህም ያለውን የሰው ኀይል አውቆ የጥቅማጥቅም እና ተያያዥ የመብት ጥያቄዎችን ለመመለስ አሠራሩ ያግዛል ነው ያሉት።
በክልሉ ከ560 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች አሉ ያሉት ወይዘሮ ካሳ ይህንን መረጃ በሚገባ በማጥራት ወደ ዲጂታል እንዲገባ ይደረጋል ብለዋል።
ይህም መረጃ መንግሥት በቀጣይ በዘርፉ ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በግብአትነት የሚያገለግል መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
