
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 12/2018 (አሚኮ) የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን መረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረማርያም በመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ ማረጋገጥ እና የሰው ኀይል መረጃን የማዘመን ሥራዎችም የሪፎርሙ አካል መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ጥራት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ አሁን ያለውን የሰው ኀይል፣ ተቋም እና መዋቅር በዲጂታል ሥርዓት መረጃዎችን ማረጋገጥ አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
በክልሉም የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ ለማረጋገጥ የታቀዱ የልማት ሥራዎችን በሚገባ በመገንዘብ ለማሳካት እንደሚያስችል ተናግረዋል። የመንግሥትን ወጭ በታቀደው መንገድ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልም ያስችላል ነው ያሉት።
መረጃው በአግባቡ እንዲጠናቀር እና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር ከተማ ሰላሟን አስጠብቃ ሰፊ የልማት ሥራዎችን እያከናወነች መኾኑን ተናግረዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንም ከተማ አሥተዳደሩ የዲጂታል አሠራሮችን እየተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ሀብታሙ ጤናው ትክክለኛ እና ወቅታዊ የሲቪል ሰርቪስ መረጃን ማደራጀት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን መረጃ በተሟላ መንገድ በመያዝ ለዲጂታል ሥርዓት ሽግግር የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ በ19 ማዕከላት እየተሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
