
ባሕርዳር: ሚያዚያ 12/2018 (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸውን ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ጠዋት የሥራ ዘመኑን ሦሥተኛ የ100 ቀናት የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ከዘጠኝ ወራት አጠቃላይ አፈጻጸም ጎን ለጎን መገምገም ጀምረናል ብለዋል።
ለእድገት አመቺ ካልነበረው እና በደካማ የተቋማት እና የፖለቲካ ማዕቀፍ ፣ በታጠረ የግል ዘርፍ ተሳትፎ፣ ውጤታማ ባልነበረ የቁጥጥር ከባቢ ከሚገለጠው የኢኮኖሚ መልክ ወጥተናል ነው ያሉት። የግሉ ዘርፍ ደካማ ውድድር ውስጥ ነበር፤ በመንግሥት ሥር የነበሩ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማትም ከፍ ባለ የዕዳ ሸክም ተዘፍቀው ከአቅም በታች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወቃል ብለዋል።
ምርታማነት አሽቆልቁሎ ኢኮኖሚውም ለአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ በሚሰጥ አዲስ ገቢር ነበብ የፓለቲካ ኢኮኖሚ መንገድ መቀየሳቸውን ገልጸዋል።
የቀየስነው አዲሱ የኢኮኖሚ አካሄድ በአጭር ጊዜ ትግበራ ጠንካራ ባለሁለት አሃዝ የእድገት ሂደትን አስመዝግቧል ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚያችን በ9 ነጥብ 2 በመቶ እያደገ ይገኛል። ይኽ እድገት በመጪው ዓመት ወደ10 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ እንጠብቃለን።
በየዘርፉም የታቀዱ ግቦቻችንን ለማሳካት ከፍ ባለ ትጋት ቀጥለን፤ በግብርና 7 ነጥብ 9 በመቶ፣ በኢንደስትሪ 13 ነጥብ 2 በመቶ፣ በአገልግሎት 9 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገቶች ሳይቆራረጡ የሚከናወኑ ይኾናል ነው ያሉት።
እነዚህ ጥረቶች የበለጠ ጽኑ፣ ተወዳዳሪ እና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለንን አቋም እና የመተግበር ዐቅም ያሳያሉ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
