
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀጣይ ግንቦት ወር እንደሚካሄድ የምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወሳል።
የሲቪክ ማኅበራት የሕዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ የምርጫ ሂደቱ ፍትሐዊ እና ታማኝ እንዲኾን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
የአማራ ሴቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ገነት ወንድሙ ሴቶች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ይመራኛል የሚሉትን ፓርቲ እንዲመርጡ ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል።
በርካታ ሴቶችም የምርጫ ካርድ በእጃቸው ይዘው የምርጫ ቀንን እየጠበቁ ይገኛሉ ብለዋል።
ፓርቲዎች ሰላማዊ ምርጫን እንዲከተሉ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲከናወን ማድረግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል። ምርጫ ካርድ የፈለጉትን መምረጥ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በተግባር የሚንጸባረቅበት መኾኑን ነው የተናገሩት።
ምርጫው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ትቅደም ወርቁ ማኅበሩ ነጋዴ ሴቶች ያላቸውን የፖለቲካ ምኅዳር በማሳደግ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ለማስቻል ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ማኅበሩ ከፖለቲካ ነጻ ኾኖ ነጋዴ ሴቶች በምርጫ የሚወክላቸውን ፓርቲ በመምረጥ በንቃት እንዲሳተፉ የተለያዩ የመረጃ አውታሮችን በመጠቀም ተሠርቷል ነው ያሉት።
“መቃወምም ኾነ መደገፍ የሚቻለው በምርጫ ካርድ ነው” ብለዋል።
ሀገርን መገንባት የሚቻለው በእያንዳንዱ ዜጋ የምርጫ ድምጽ እንደኾነም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
