አነባበሮ የኾነው የሕወሃት ጥፋት!

31

 

ብዙዎች የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ጥፋቱ ወጣቶችን ለጦርነት እያስገደደ ወደ ማሠልጠኛ መውሰዱ ብቻ ይመስላቸዋል።

የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ጥፋት ግን ከዚያም በላይ እጥፍ ድርብ ነው። የቡድኑ የመጀመሪያው ጥፋት በእርግጥም ለአቅመ ጦርነት ያልደረሱ ወጣቶችን እያስገደደ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ማድረጉ ነው።

ሌላው የሕገ ወጥ ቡድኑ ጥፋት እነዚህ ወጣቶች ለጦርነት የሚገደዱት መዳረሻዬ ካሉት ህልማቸው እየተናጠቡ ነው ። ለምሳሌ ተምሮ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለት፣ መሐንዲስ ወይም ሌላ የመኾን ህልም ያላቸው የትግራይ ወጣቶች ለሕገ ወጥ ቡድኑ የሥልጣን መቆየት ሲሉ ህልማቸውን ይነጠቃሉ።

የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን በግዴታ ሲነጠቁ የሚያጡት ጧሪዎቻቸውን ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ተስፋቸውን እና የስማቸውን (ዘራቸውን ) መቀጠልም ጭምር እንጂ።

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የአማራን ሕዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ደጃፉ ድረስ ሄደው የፈጸሙበት የጭካኔ ድርጊት ነገ በሌላውም ኢትዮጵያዊ ላይ ላለመፈጸሙ ዋስትና ስለሌለው ከእነሱ ብሔር ውጪ የኾነ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ምድር እንዲኖር ወይም እንዳይኖር ፈቃጅ እንሁን ማለታቸውም የጥፋቱ አንድ አካል ነው ።

ሕገ ወጥ ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ ጦርነት ባሕላዊ ጨዋታው ነው እያሉ የትግራይ ሕዝብን ሃይማኖተኝነት፣ ሰው ወዳድነት፣ ባሕል አክባሪነት፣ የኢትዮጵያ መሠረትነት እና ሌሎችንም ትውፊቶቹን መንጠቃቸውም ሌላው የጥፋታቸው ንብብሮሽ ነው።

የትግራይ ሕዝብ የአክሱም ተሳላሚ እና የነጃሺ ሰጋጅ እንጂ ሃይማኖተኛ እንጅ እንደ ሕወሃት ጦርነትን አምላኪም አይደለም።

የትግራይን ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት ክደው ከኢትዮጵያ እና ከሕዝቧ ጋር መጋጨትን ከመንግሥት ጋር ብቻ እንደመጋጨት ማሰባቸውም ሌላኛው ስህተታቸው ነው ።

ሕገ ወጥ ቡድኑ ኢትዮጵያን ከመውጋታቸውም ባለፈ ኢትዮጵያን ከሚወጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር መነባበራቸውም ሌላው መለያቸው ነው ።

ንብብሮሹ ሲቀጥል የትግራይን ሕዝብ በስሙ እየማሉ እና እየተገዘቱ ያገኙትን እርዳታ ከጉሮሮው በመንጠቅ ለጦርነት የሚያውሉ ጨካኞች ስብስብም ነው።

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን እነሱ ብቻ የማይመሯት ኢትዮጵያ ከኾነች የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነቱ ተነጥሎ ትግሬ ብቻ ኾኖ እንዲኖር የሚፈልጉም ናቸው ።

ለጊዜው ከሁሉም የከፋው ግን በግፍ የሚፈሰው የትግራይ እናቶች እንባ ነው። ምክንያት አልባ ለኾነ ጦርነት አካላቸውን ለሚያጡ እና ሕይወታቸውን ለሚገብሩ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ሲባል ጦርነት ጠማቂዎችን ለይቶ በቃችሁ ማለት ይገባል።

የትግራይ እናቶች እንባ በጉንጫቸው ላይ ብቻ መፍሰስ የለበትም፤ ይልቁንም እንባቸው የዓለም ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በሙሉ መድረስ እና እውነተኛ ፍትሕ ማግኘት አለባቸው።

የትግራይ ወጣቶች የመማር፣ በሰላም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እና ሌሎችም ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሊከበሩላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግሥትን ጨምሮ የአፍሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ እጃቸውን ሊዘረጉ ይገባል። ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድንም በሕግ አግባብ መቀጣት ይኖርበታል። ያኔ ኢትዮጵያ ሰላም ትህናለች፤ ሕዝብም በሰላም እና በፍቅር ሰርቶ ያድጋል።

#አሚኮ_ዜና #Ethiopia #peace
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_12_2018 ዓ.ም

በእሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ይህ ቀን ቀደምት ትውልዶች በሀገራችን እውን ኾኖ ለማየት ሲመኙት የነበረ ግን ያልታደሉት ታሪካዊ ቀን ነው” አቶ ሰለሞን አየለ
Next articleከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመላው ኢትዮጵያዊያን የተላለፈ መልዕክት!