
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤዋን እያካሄደች ነው። በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ታላቅ ተስፋን ሰንቃለች። በጉባኤው ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሰለሞን አየለ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሀገራችን ሕዝቦች ሲጠይቁት እና ሲጠብቁት የኖሩት ነው ብለዋል። ይህ ቀን ታሪካዊ ቀን ነው፣ ይህ ቀን ቀደምት የሀገራችን ትውልዶች በሀገራችን እውን ኾኖ ለማየት ሲመኙት የነበረ ግን ያልታደሉት ታሪካዊ ቀን ነው ብለውታል።
የተለያዩ የፖለቲካ ኀይሎች በተለያየ ዘመን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሀገራዊ መግባባት እውን እንዲኾን ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ እውን የኾነበት ታሪካዊ ቀን ነው፤ ይህ ቀን የፖለቲካ ሥልጣን በጠመንጃ ሳይኾን በሠለጠነ ፖለቲካ በሕዝቦች ፍላጎት የሚገኝበትን የመሠረተ ድንጋይ የምንጥልበት ነው ብለዋል።
ሀገርን ከግጭት እና ከእርስ በእርስ መገዳደል አዙሪት አላቆ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት የሚያስችለንን የፖለቲካ ባሕል ለመገንባት አንድ ብለን የምንጀምርበት ነው፤ መጭው ትውልድ ሲያስታውሰው የሚኖር የሀገራችን መጻዒ ዕድል የሚወስን ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከምሥረታው ቀን ጀምሮ ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ ሢሠራባቸው ከቆዩት ጉዳዮች መካከል ሀገራዊ ምክክር እና ሀገራዊ መግባባት ዋነኛው መኾኑን ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የመቋቋሙ ዋና ምክንያት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሀገርን ለማጽናት መኾኑን አንስተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሀገራዊ ምክክሩ እውን እንዲኾን ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ብሔራዊ መግባባት የፖለቲካ አለመረጋጋትን በማስቀረት፣ ግጭትን እና ጦርነትን ለማስቆም እና የፖለቲካ ችግግርን በተሳካ ሁኔታ ለመፍታት በአንድ ሀገር ባለቤትነት የሚካሄድ የፖለቲካ ሂደት መኾኑን አንስተዋል።
ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ልዩነቶች አውዳሚ እንዳይኾኑ በማድረግ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ከቃል አልፎ በተግባር እንዲገለጥ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል። የጋራ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ ችግሮች ለመፍታት ምክክር ተደርጎ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረስ አለበት ብሎ ያምናል ነው ያሉት።
የጋራ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን፣ በፖለቲካ ኀይሎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር፣ አዲስ የሠለጠነ የፖለቲካ ሃሳብ ውቅር ለመንደፍ፣ በዜጎች እና በመንግሥት መካከል አዲስ ማኅበራዊ ውል እውን እንዲኾን ሀገራዊ ምክክር ብቸኛው የፖለቲካ መፍትሔ እንደኾነም በጽኑ ያምናል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ ምክክር እውን እንዲኾን የበኩሉን ተወጥቷል፤ እስከ ፍጻሜውም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። የጋራ ምክር ቤቱ አካታች እና አሳታፊ ውይይት እንዲደረግ ሢሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት ነጻ ኾኖ በገለልተኛ አካል ይመራ ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።
የመወያያ አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ሕልውና የሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች በመኾናቸው አከራካሪ መኾናቸው አይቀርም፤ ሁሉም የተለያየ ዕይታ እና አረዳድ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፤ በእነዚህ ሀገራዊ በኾኑ አጀንዳዎች ዙሪያ መግባባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሀገርን መጻዒ ዕድል በሚወስኑ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት ታሪካዊ ኀላፊነት እና ተጠያቂነት ያለበት መኾኑን መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል። በአጀንዳዎቹ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ከራስ እሳቤ ባሻገር የሌሎችንም መስማት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የተጀመረው ውይይት የተሳካ እንዲኾን ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት። በምክክር ሀገርን በጋራ እናጽና ብለዋል በመልዕክታቸው።
#አሚኮ #ሀገራዊምክክር #Ethiopia
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
