ለጸናች ሀገር፤ የበሰለ ምክክር !

10

 

ኢትዮጵያን ያጸኗት ልጆቿ ናቸው፡፡ ከውጭ ጠላት የተከላከሉላት፤ በነጻነት ያኖሯት፤ ሉዓላዊነቷን ያስከበሯት ልጆቿ ናቸው፡፡ ዓድዋን የመሰለ ድል ያስገኙላት፤ የቅኝ ገዢዎችን አንገት ያስደፉላት፤ በአፍሪካ ምሳሌ እና አርዓያ አያደረጓት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

የሀገር ፍቅር እየጠራቸው፤ አንዲት ሠንደቅ ዓላማ እያሰባሰበቻቸው አንድነታቸውን አጠንክረው ከጠላቶች ጋር ተፋልመዋል፡፡ ሀገራቸውን ከጠላት መንጋጋ ጠብቀዋል፡፡ እየወደቁ ሀገር አጽንተዋል፤ ደማቸውን እያፈሰሱ፤ አጥንታቸውን እየከሰከሱ የሀገርን ክብር ለዘመናት አስከብረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውን የአፍሪካ አርዓያ እና እናት ያደረጓት በአንድነታቸው ነው፡፡

ጠላት ኢትዮጵያን ሊወርር ሲመጣ ንጉሠ ነገሥት እምዬ ምኒልክ ‌አዋጅ ሲያስነግሩ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር የተንቀሳቀሱት፤ በባዶ እግራቸው ጠላት መጣበት ወደተባለው ሥፍራ የገሰገሱት፤ በጀግንነትም ተዋግተው ጠላታቸውን ድል መትተው ዓድዋን የመለሰ ከተራራ የገዘፈ ታሪክ የሠሩት ለሀገራቸው ባላቸው ቀናዒነት ተነስተው ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም ሀገር ስትጠራቸው መሳበሰብን፣ በአንድነት መጽናትን ያውቁበታል፡፡
ሀገራቸውን ለውጭ ጠላት አናስነካም ብለው ለዘመናት በጽናት የኖሩት ኢትዮጵያውያን ከውስጥም ከውጭም ጠላት አጥቷቸው አያውቅም፡፡ ሁልጊዜም ይፈትናቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የተረጋጋ ሰላም እያጡ ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡

ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ዐጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው የኛ የኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪክ እጅግ ያሳዝናል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ፍጹም የኾነ ሰላም አግኝተን አናውቅምና ይላሉ።

የተወደደች ሀገራችን ዘወትር በጠላቶች ተከባ ስትኖር ነበረች ትኖራለችም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የውጭ ጠላት ከዚህ በፊት አላዋረደንም። አንድ ስንኾን ምንም የሚደፍረን እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል።

ዘወትር በስምምነት እና በፍቅር ኖረን ብንኾን ኖሮ እስከዛሬ ድረስ ብዙውን ትልልቅ ነገር መፈጸም እንችል እንደነበር ጥርጥር የለውም ይላሉ፡፡ ሌሎች ሕዝቦች በአዕምሮ እና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደኋላ ቀረን፤ የዱሮውም ያሁኑም ኑሮዋችን እጅግ ያሳዝናል። በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ እኛ እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም። ሌሎች እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው በአንድነት ኾነው ሲደክሙ እኛ አንድ ዘር እና ወንድማማች መኾናችንን አልተገለጸልንም። እርስ በእርሳችን መፋጀትም እስከዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል ብለው ጽፈዋል፡፡

አሁን ግን ከዘመናት ድካም በኋላ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ከመፋጀት የሚወጡበትን ዘዴ ዘይደዋል። ችግሮቻቸውን በምክክር ለመፍታት በአንድ አደራሽ ተሰባስበዋል። በተሰባሰቡበት አደራሽ ውስጥ ከምሥራቅ ንፍቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን ንፍቅ እስከ ደቡብ ድረስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተወክለዋል። በዚህ አዳራሽ ውስጥ ኢትዮጵያ ትገለጻለች። ኢትዮጵያም ተወክላለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ትናንት ጀምሯል። በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ደስ ተሰኝታለች። ተስፋንም ሰንቃለች።

በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት ከሐመር ካራ ብሔረሰብ ተወክለው የመጡት ሙዶ አኮ ልቤ በተስፋ ተመልቷል፤ ለብዙ ዘመናት እንደእኛ ያሉ ሴቶች ከሩቅ ቆመን እንመለከት ነበር፤ ሌሎች ይናገሩ ነበር፤ ሌሎች ይወስኑ ነበር፤ እኛ ግን ከሩቅ ቆመን እናይ ነበር ነው ያሉት።

እንባችንን እናፈስስ፤ ሰላም ይመጣ ይኾን ብለን እንጠይቅ ነበር፤ ዛሬ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሬ እንድናገር ጠርታኛለች ብለዋል፡፡ ይህ ንግግራቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን አካታችነት እና አሳታፊነት በግልጽ ያሳያል፡፡

ይህ ድምጽ የእኔ ብቻ አይደለም፤ ከሩቅ ያሉት ሴቶች እና እናቶች ድምጽ ነው ይላሉ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ እያዳመጠች ነው የሚሉት ሙዶ አኮ ባለመነጋገራችን ብዙ አጥተናል፤ ባለመነጋገራችን ያተርፍነው ሀዘን፣ ለቅሶ፣ ጥላቻ እና በቀል ነው ብለዋል። እሳት ቤት ቢገነባ ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት በተገነባች ነበር፤ ነገር ግን ቤት የሚገነባው እጆች ሲተባበሩ እና ልቦች ሲደማመጡ ነው ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ የእኔ፣ የእኛ፣ የእናንተ የሁላችንም ናት፤ ወገኖቼ ይዛችሁት የመጣችሁትን ቁጣ እና ቋጠሮ ይዛችሁ አትመለሱ። ተመካክራችሁ ፍቱ፤ ማን ያሸንፋል ብለን አንጠይቅ፤ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ፤ የብዙ እናቶች ሕልም ይህ ነውና ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሀገራችን ሕዝቦች ሲጠይቁት እና ሲጠብቁት የኖሩት ነው ይላሉ። ይህ ቀን ታሪካዊ ቀን ነው፤ ይህ ቀን ቀደምት የሀገራችን ትውልዶች በሀገራችን እውን ኾኖ ለማየት ሲመኙት የነበረ ግን ያልታደሉት ታሪካዊ ቀን ነው ብለውታል።

የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያየ ዘመን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሀገራዊ መግባባት እውን እንዲኾን ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ እውን የኾነበት ታሪካዊ ቀን ነው፤ ይህ ቀን የፖለቲካ ሥልጣን በጠመንጃ ሳይኾን በሠለጠነ ፖለቲካ በሕዝቦች ፍላጎት የሚገኝበትን የመሠረተ ድንጋይ የምንጥልበት ነው ብለዋል።

ሀገርን ከግጭት እና ከእርስ በእርስ መገዳደል አዙሪት አላቆ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት የሚያስችለንን የፖለቲካ ባሕል ለመገንባት አንድ ብለን የምንጀምርበት ነው፤ መጪው ትውልድ ሲያስታውሰው የሚኖር የሀገራችን መጻዒ ዕድል የሚወስን ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው። ኢትዮጵያ ድሮም የተጠበቀችው በልጆቿ ነው። ዛሬም ችግሮቿን የምትፈታው በምክክር ነው። ለጸናች ሀገር፤ የሰከነ ምክክር ያስፈልጋል፤ ይሄንም ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ነው።

#አሚኮ #ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ🇪🇹 #ባሕር_ዳር #ሐምሌ12_2018_ዓ_ም

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየደም እንባው ሳይደርቅ የተፈጸመ ክህደት!
Next article“ይህ ቀን ቀደምት ትውልዶች በሀገራችን እውን ኾኖ ለማየት ሲመኙት የነበረ ግን ያልታደሉት ታሪካዊ ቀን ነው” አቶ ሰለሞን አየለ