ሚዲያው የሰላም እንጂ የሁከት ምንጭ መኾን የለበትም።

9

 

አዲስ አበባ: ሚያዚያ 10/2018 (አሚኮ) “የሃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኀን ለሰላም እና አብሮነት” በሚል መሪ መልክት የውይይት መድርክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ፤ የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኀን ለማኅበረሰቡ በተለይም ለሃይማኖቱ ተከታዮች ተደራሽ በመኾን ሃይማኖታዊ አስተምህሮታቸውን ከማድረስ ጎን ለጎን እንደ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ እህትማማችነት እና ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ልማት እና መሰል የሁሉም ሃይማኖቶች የጋራ እሴት የኾኑትን ሃይማኖታዊ ተግባራት በማኅበረሰቡ ዘንድ በማስረጽ ረገድ ሰፊ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኀን በጋራ በመኾን የራሳቸውን ማኅበር በማቋቋም የሃይማኖት ሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎቻቸው የሚመሩበትን የኤዲቶሪያል አሠራር እና የሥነ-ምግባር ደንብ እንዲያዘጋጁም በዚሁ መድረክ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ሃይማኖት ፍቅር ነው፣ ሃይማኖት አብሮነት ነው፤ ሃይማኖት መተሳሰብ ነው፤ ይህንን እሴት ደግሞ በሚዲያዎቻችን አማካኝነት ለተከታዮቻችን ብሎም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች ማድረስ መቻል አለብን ብለዋል።

ሚዲያው የሰላም እንጂ የሁከት ምንጭ መኾን እንደሌለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሚዲያዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲቆጣጠሩ፣ የሥነ-ምግባር ደንቦችን እንዲያወጡ እና በዚያው መሠረት እንዲመሩ ድጋፍ እንደሚደረግም ከመድረኩ ተነስቷል።

በዚሁ መድረክ የተገኙ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኀን ተቋማት ባለሙያወች እና የሥራ ኀላፊወች ” በዚህ ደረጃ ሥራዎቻችን ቀርበው ውይይት ማድረጋችን መልካም ነው” ብለዋል። በቀጣይ የታዩ ክፍተቶችን ለመሸፈን የሚያግዙ ሥልጠናወች እና መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ 51 የሃይማኖት መገናኛ ብዙኀን ተቋማት እንዳሉ የተገለጸ ሲኾን 39 የሳተላይት ስርጭት ላይ ያሉ ናቸው ቀሪ 12 ደግሞ ከሳተላይት ስርጭት ውጭ መኾናቸው ተመላክቷል።

በዚሁ መድረክ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን በሚንቀሳቀሱ የጽንፈኛ ቡድኑ አመራሮች እና አባላት ላይ እርምጃ ተወሰደ።
Next articleመቃወምም ኾነ መደገፍ የሚቻለው በምርጫ ካርድ ነው።