“ዛሬ የምንገነባው ለነገው ትውልድ ኩራት እና የብልጽግና ዋስትና ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

4

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንትን አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ እየተገነባች ነው ብለዋል።

ዛሬ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት በደማቅ ሥነ ሥርዓት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

መሠረተ ልማት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ግብአቶችን በማመላለስ የኢኮኖሚያችን የደም ሥር፣ የብልጽግናችን መሠረት ነው። በዐውደ ርዕዩ የተመለከትነውም ወሳኝ የልማት ተቋሞቻችን፣ መሠረተ ልማትን እንደ ሀገር በቅንጅትና በትብብር የመምራት አዲስ የሥራ ባሕል እየገነቡ መኾናቸውን ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ፈጠራን፣ ፍጥነትን እና ጥራትን የጉዟችን መርሕ አድርገን በመሥራት ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግበናል ነው ያሉት ። የመንገድ ርዝመታችንን በብዙ ኪሎ ሜትሮች አሳድገናል፤ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት ዐቅማችንን ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት አካባቢ አድርሰናል። በዲጂታል ዘርፍም የሞባይል ተጠቃሚዎችን 97 ሚሊዮን እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 57 ሚሊዮን አድርሰናል ብለዋል።

በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎቻችን “ከተባበርን የማይቻል የለም” የሚለውን መርሐችንን በተግባር ያሳዩ፣ ፍጥነትና ጥራትን ያስተሣሠሩ ፕሮጀክቶች ናቸው።

ጉዟችንን ለማጣጣል ለሚሞክሩም ኾነ “የውጤቱ ባለቤት እኛ ነን” ለሚሉ ሁሉ መልሳችን አንድ ነው፤ እውነታውንና ፍርዱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትተን፣ ሥራችንን እንቀጥላለን! ኢትዮጵያን ለማበልጸግና ለመገንባት በየበረሃውና በየተራራው እየፈሰሰ ላለው ላብና ደም ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ነው ያሉት።

መንግሥት በመንገድ፣ በኃይል፣ በመስኖ፣ በባቡርና በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፍ ፈጣንና ፍትሐዊ ልማት ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት የሥራ፣ የውጤት እና የተስፋ ዘመን ነው። ትናንት የተገነባው ለዛሬ፣ ዛሬ የምንገነባው ደግሞ ለነገው ትውልድ ኩራት እና የብልጽግና ዋስትና ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከኢራን ጋር የሚደረጉ ንግግሮች በፍጥነት ሊጠናቀቁ መቃረባቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።
Next article📈 3 ሺህ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች በአማራ ክልል