
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2018/19 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን የሰበል ልማት እና ጥበቃ የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው የግብርናው እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያመጣ መኾኑን ተናግረዋል። ግብርናውን ከዕለት ፍጆታ ባሻገር ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ ታሳቢ በማድረግ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ክልሉ በኩታ ገጠም ምርት ውጤታማ እየኾነ መምጣቱን አንስተዋል። ግብርናውን የበለጠ ለማሳደግ ምርጥ ዘርን በአግባቡ መጠቀም እና ቴክኖሎጂን ማስፋት እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት። የአማራ ክልል እንደ ሀገር ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ሰፋፊ የኩታ ገጠም ልማቶችን ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ የ2017/18 የምርት ዘመን ስኬታማ እንደነበር አስታውሰዋል። ምርታማነትን ማሳደግ መቻላቸውንም ተናግረዋል። ምርታማነት በሄክታር ከነበረበት ከ32 ነጥብ 2 ኩንታል ወደ 34 ነጥብ 9 ኩንታል ማድረስ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
ለክልሉ እድገት የግብርናው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉን የኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ የሚወስደው ግብርና መኾኑን አንስተዋል። በቀጣይም ምርት እና ማርታማነትን ከዚህ በላይ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ምርትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ካስቀመጥነው ግብ በላይ ማሳካት ችለናል ያሉት አሥተባባሪው 187 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት አቅደን ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ 188 ሚሊዮን ኩንታል አምርተናል ብለዋል።
በ2018/19 የመኸር ምርት 5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን ገልጸዋል። ምርታማነትን በሄክታር ለማሳደግ እና ዕቅዱን ለማሳካት ብርቱ ጥረት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን እና ከልማዳዊ አሠራር ማውጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ዕቅዱን ለማሳካት አርሶ አደሮች ምርታ እና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ማቀናጀት ይገባል ነው ያሉት። በተበታተነ አሠራር ውጤታማ መኾን እንደማይቻልም ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችን በማደራጀት ማሳውንም በኩታ ገጠም እና በተቀናጀ መንገድ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። የተሟላ የቅድመ እና የድህረ ምርት ክትትል ለማድረግ ኩታገጠም ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ዓመት ለግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት በልዩ ትኩረት መሥራት አለብን ነው ያሉት። በተለመደው አሠራር ብቻ የተፈለገው ምርት እንደማይሳካ ነው የተናገሩት።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ማዳበሪያን በተገቢው ማሠራጨት፣ የምርጥ ዘር አጠቃቀምን ማሳደግ እና ቴክኖሎጂን ማዘመን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ግብርናው አሁን ላይ ተደራራቢ አደራ እና ግብ እንደተጠላበት ተናግረዋል። ግብርናውን ከእጅ ወደ አፍ በማላቀቅ ከፍ ያለ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከኢኮኖሚ ባርነት ለመውጣት ግብርናው ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። በቅንጅት ከሠራን ያቀድነውን እናሳካለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
