
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የተመራ ልዑክ በተመረጡ የአውሮፓ እና የኤዥያ ሀገራት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማትን የሥራ ጉብኝት ሲያደርግ ቆይቷል።
የሥራ ጉብኝቱ ዋና ዓላማ በሀገር እና በክልል ደረጃ የተጀመሩ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ላይ የለውጥ ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር እንደኾነ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል።
በቀጣይ በተመረጡ መስኮች ላይ ከተቋማቱ ጋር በትብብር መሥራት የሚቻልበትን ምቹ መደላድል መፍጠር እንደኾነም ነው የተናገሩት። ውጤታማ ጉብኝት እና ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
የልዑክ ቡድኑ አባላት በሲንጋፖር፣ በሆንግ ኮንግ፣ በፈረንሳይ እና በኔዘርላድ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን ጎብኝተዋል፤ ውይይትም አድርገዋል።
የሲንጋፖር ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል፣ ማክስ ዌል ቻምበር እና የሲንጋፖር ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጎብኘት ሥራ ተከናውኗል።
በሆንግ ኮንግ፤ የሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከልን፣ ዓለም አቀፍ የሽምግልና ማዕከልን፣ የሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ የሕግ ማሠልጠኛ ተቋምን እና የሆንግ ኮንግ ዲፓርትመንት ኦፍ ጀስቲስን እንዲሁም፤ ከአውሮፓ ሀገራት የፈረንሳይ ሁለት ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከላትን፤ በኔዘርላድስ ዓለም አቀፍ ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤትን እና በዘ ሄግ ዓለም አቀፍ የሕግ ትምህርት ተቋምንም ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ከየሀገራቱ የተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ጋርም ውይይት ማድረጋቸውም ነው የተገለጸው።
አቶ ዓለምአንተ አግደው በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ እና የተሠሩ ሰፋፊ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እና ሁለንተናዊ የተቋም ግንባታ የለውጥ ሥራዎች፣ ተደራሽ እና ውጤታማ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት እና ፍርድ ቤቶችን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።
የዓለም አቀፍ ተቋማቱ መሪዎች በበኩላቸው እንደ ሀገር በኢትዮጵያ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ እንዲሁም በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ውጤታማነት አድንቀዋል። በቀጣይ በባለሙያ አቅም ግንባታ፣ በቴክኒክ ድጋፍ እና ልምዶችን በማጋራት ረገድ አብሮ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎትም ገልጸዋል።
የልዑክ ቡድኑ የሥራ ጉብኝቱን አጠናቅቆ ተመልሷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
