
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ የጎበኙት በደዋ ጨፋ ወረዳ ገርቢ እና ሸክላ ቀበሌዎች ሚላ ሚሌ እና ኮዮ የለማ የሙዝ ክላስተርን ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በቀጣናው አስተማማኝ ሰላምን የማጽናት ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ሲጠነሰሱ የነበሩ ሴራዎችን በማክሸፍ ዘላቂ ሰላምን፣ አንድነትን እና ወንድማማችነትን የማጠናከር ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰላም እንዲረጋገጥ ያደረጉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችን አመስግነዋል። ከሰላም ማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችም እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። የአካባቢው ሕዝብ በልማት የሚታወቅ መኾኑንም አንስተዋል።
አካባቢው በአትክልት እና ፍራፍሬ ትልቅ ጸጋ እንዳለው ነው የገለጹት። ያለው እምቅ አቅም ከአካባቢው አልፎ ለክልሉ እና ለሀገር የሚተርፍ ነው ብለዋል። ለውጭ ገበያ የሚቀርብ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
በክልሉ የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርቶችን ለማስፋት በዕቅድ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ጽንፈኞችን እየተከላከለ ሰላምን እያረጋገጠ መኾኑን ነው የገለጹት። ጽንፈኝነትን ተዋግታችሁ ሰላማችሁን ስላረጋገጣችሁ እናመሰግናችኋለን ብለዋል። የተጀመረውን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል። የተገኘውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአፋር ወንድሞቻችን በሰላም እና በልማት ሥራዎች አብረውን ለመሥራት ቆርጠው ተነስተዋል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
“የበለጠ ሰላማችን እንጠብቅ፤ የሰላም እጦት አይጠቅምም፤ የሚጠቅመን ልማት እና ብልጽግና ነው” ብለዋል።
ሥልጣን የሚገኘው በምርጫ ነው በማለት በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በርካታ ዜጎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ለዚህ ዴሞክራሲያዊ አካሄድም ምስጋና ይገባችኋል ነው ያሉት።
ያለውን ሃብት በአግባቡ ተጠቀሙበት፤ የበለጠ አልሙ ብለዋል።
የአፋር ወንድሞቻችን አብረናችሁ ነን ብለው ከእኛ ጋር ተገኝተዋል፤ የሁለቱን ክልል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በማጠናከር እድገታችንን እናረጋግጣለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
