
ባሕር ዳር ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ቆላድባ ከተማ ሴቶች በንቃት የመራጭነት ካርዳቸውን እያወጡም ይገኛሉ።
ከምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ምርጫ ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ መኾኑን በመገንዘብ በንቃት ለመሳተፍ የመራጭነት ካርዳቸውን መውሰዳቸውን የከተማዋ ነዋሪ ሴቶች ገልጸዋል።
ሌሎች ሴቶች በቀጣይ ሀገራዊ ምርጫ የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ እንዲወስዱም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ምርጫ የቀጣይ ዕድልን የሚወስን በመኾኑ ሁሉም ሴቶች መብታቸውን ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የምርጫ ካርድ መውሰድ እና ድምጽ መስጠት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከቤታቸው እና ከአካባቢያቸው መጻዒ የልማት ዕድል ጋር የተያያዘ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የምንፈልገውን ፓርቲ በካርዳችን መምረጥ ከቻልን ድምፃችን ለሀገራችን ዕድገት፣ ሰላም እና ልማት የሚመጥን አገልግሎት እንድናገኝ ያስችለናል ብለዋል።
ሁሉም ሰው ካርድ በጊዜው በማውጣት፣ በምርጫ ሂደት ላይ በንቃት ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
