
ደሴ: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ7ኛው ሀገራዊ አጠቃላይ ምርጫ “ለሀገር ይበጃል፣ ሀገርን ይመራል” የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ መኾናቸውን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና ሀገረ መንግሥት ለመገንባት በምርጫ መሳተፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አብዱ ኢብራሂም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ምርጫ ወሳኝ መኾኑን ጠቅሶ፤ በተለይም ወጣቶች በምርጫው ሂደት ላይ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ መክሯል።
ሌላዋ የከማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሀና በዛብህ በምርጫ መሳተፍ የሥልጡን ማኅበረሰብ መገለጫ መኾኑን አስረድተዋል። “ለነገው የልማትም ኾነ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎቻችን ምላሽ ለማግኘት ዛሬ ላይ በምርጫ መሳተፍ እና ድምጽ መስጠት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ወጣት ሰይድ ይመር በበኩሉ ምርጫ ዋነኛው የዴሞክራሲ መለማመጃ መድረክ መኾኑን ጠቁሞ፤ ሀገርን በብቃት ያስተዳድራል የሚሉትን ፓርቲ መምረጥ የዜጎች የሀገርን ዕጣ ፈንታ የመወሰን ትልቅ ዕድል መኾኑን ገልጿል።
ነዋሪዎቹ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
