
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ እና ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ መሪዎች በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ የጎበኙት በደዋ ጨፋ ወረዳ ገርቢ እና ሸክላ ቀበሌዎች ሚላ ሚሌ እና ኮዮ የለማ የሙዝ ክላስተርን ነው።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የአካባቢው ሕዝብ ሰላሙን በማረጋገጡ ወደ ልማት ዞሯል ብለዋል። አካባቢው የአንድነት፣ የኅብረ ብሔራዊነት እና የፍቅር ተምሳሌት መኾኑንም ገልጸዋል።
ከአጎራባች ዞኖች ጋር በጋራ ሰላምን በማረጋገጥ ወደ ልማት መግባታቸውን ነው የተናገሩት። በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጉዞ የሚያሳልጡ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በአካባቢው ትልቅ የፍራፍሬ ጸጋ እንዳለ አንስተዋል። ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የጀመርናቸውን ሥራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዞኑ የአትክልት እና ፍራፍሬ ውጤታማ እንዲኾን ላደረጉ መሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) ኢትዮጵያ መልማት የሚችል ብዙ ጸጋ እንዳላት ተናግረዋል። በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደግሞ መልማት የሚችል እምቅ ጸጋ አለ ብለዋል።
ግብርና ሚኒስቴር የመልማት ጸጋዎችን እየለየ ውጤታማ ሥራ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል። በአትክልት እና ፍራፍሬ የታየው ለውጥ የሚደነቅ መኾኑን ነው የተናገሩት። መሪዎች ግብርናን በተገቢው መንገድ እየደገፉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። አስደናቂ ልማት ስላሳያችሁን እናመሰግናችኋለን ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
