በአማራ ክልል የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ 196 የጤና ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው።

8
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት የጤና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ለማኅበረሰቡ ሁሉን አቀፍ፣ ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግሥት በጀት መድቦ በተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ የጤና ተቋማትን በመገንባት እና በነባር ሆስፒታሎች ላይ የማስፋፊያ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በአጠቃላይ 196 ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ሲኾኑ ከእነዚህም መካከል 23ቱ ትልልቅ የጤና ፕሮጀክቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት፦
👉7 አዳዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣
👉2 ጠቅላላ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም
👉3 የማስፋፊያ ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ኀላፊው አክለውም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የ17 የጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ግንባታ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጋዝ ጊብላ ወረዳ አስ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የጋዝ ጊብላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በግንባታ ላይ የሚገኝ እና አንዱ ተጠቃሽ ፕሮጀክት ስለመኾኑም አስረድተዋል። ግንባታው በ2012 ዓ.ም ቢጀመርም በቁሳቁስ ዋጋ ንረት፣ በሰላም እጦት እና መሰል ችግሮች ምክንያት ተስተጓጉሎ ቆይቷል ነው ያሉት። ኾኖም ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ውይይት ግንባታው ዳግም ተጀምሮ አሁን ላይ 70 በመቶ መድረሱን አቶ አብዱልከሪም አረጋግጠዋል።
የዓባይ ኮንስትራክሽን የፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ጥላ ተፈራ በበኩላቸው፤ ግንባታውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ገነት ሰፊው ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ ከ130 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና የነበረውን የሪፈራል እንግልት እንደሚቀርፍ አስረድተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ቀደም ሲል ለሕክምና ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው የሆስፒታሉ ግንባታ መጠናቀቅ ለዓመታት የቆየውን ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾንም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኢትዮጵያ የሳይበር ወንጀልን ለመከላከል ምን አለ?
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን ተመለከቱ።