“ወሎ ማለት ኅብር ማለት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

21
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ፕሮጄክት ተጠናቅቆ መመረቁ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የሪዞርቱ ሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ፕሮጄክቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።
ይህ ፕሮጀክት የመደመር እሳቤ ውጤት መኾኑን ተናግረዋል። በዚህ ፕሮጄክት የኢትዮጵያውን አስተዋጽኦ አለበት፤ ይህም ስንደመር ምን እንደምናሳካ ማሳያ ነው ብለዋል።
በዚህ ስፍራ ከቆቦ እስከ መካነ ሰላም፣ ከዋግ እስከ ከሚሴ፣ ከተከዜ እስከ ዓባይ ሸለቆ ድረስ ያሉ ሰዎች ታድመዋል፤ በአንድነት የተሠባሠበው ይህ ሕዝብ ከተባበረ ይህን አካባቢ የሃብት ቀጣና ማድረግ ይችላል ነው ያሉት።
ወሎ ማለት ኅብር ማለት ነው፣ ቋንቋው፣ ታሪኩ፣ ባሕሉ ኅብር ነው፤ ይህን ሥርዓት የበለጠ ኅብር የሚያደርገው የአፋር ወንድሞቻችን በመምጣታቸው ነው ብለዋል።
የወሎ አካባቢ የሌለው ሃብት እንደሌለም ተናግረዋል። አካባቢው በጸጋ የታደለ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የመሰለ ጸጋ ይዘን እንዴት ስለ ችግር እናወራለን? የወሎን መሬት ካለማነው አብዝቶ ይሰጠናል፤ ግን ሳናለማው ኖረናል፣ አሁን ግን ዐይን ገላጭ ሥራ አይተናል፤ ማልማት አለብን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ማለት የወሎን አፈር ተጥቅሞ ምርጥ ምርት ማምረት ማለት ነው ብለዋል። አካባቢው በርካታ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች እንዳሉትም ተናግረዋል። ሪዞርቱ ለቱሪዝም መዳረሻነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ሀገር የሚሠራው በመንግሥት እና በግል ትብብር መኾኑንም ገልጸዋል። የሚያዋጣን የራሳችን ሃብት በአግባቡ መጠቀም ነውም ብለዋል። ከሌሎች መጠየቅ እና ማምጣት አይጠቅምም፤ ሲቆም ይቆማል፤ የሚጠቅመን የራሳችንን ሃብት መጠቀም ነው ብለዋል።
በአካባቢው የሙዝ ልማት እየለማ መኾኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጆቻችን ጫት ሳይኾን ሙዝ እንዲመገቡ እንፈልጋለን ነው ያሉት። የጀመርናቸው ሥራዎች እዚህ የደረሱት አንጻራዊ ሰላም ስላለ ነው፤ ሰላም ልማትን፤ ልማትን ሰላም ያመጣል፤ ሰላማችሁን አጥብቃችሁ እንድትይዙ አደራ እላለሁ ብለዋል።
መጭው ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል። ተጨማሪ ልማቶች እንደሚሠፉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“አንድ ፕሮጄክት ሲጠናቀቅ ሌሎች መልካም ነገሮችን ይስባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ