
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ፕሮጄክት ተጠናቅቆ መመረቁ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የሪዞርቱ ሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመቻቻል፣ የፍቅር እና የሥራ ወዳድ ተምሳሌት በኾነው በወሎ ምድር እንዲህ አይነት ፕሮጄክት በመሠራቱ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
እስካሁን ያላየናቸው ሃብቶች እየተለዩ ወደ ተጨባጭ አቅም እየተቀየሩ ናቸው ነው ያሉት። የልማት ጸጋዎችን እንድናይ ላደረጉን እና ሠርተው ላሳዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ፕሮጄክቱ ባማረ ሁኔታ መገንባቱንም ተናግረዋል። ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ እንዲህ አይነት ሥራ በመሥራታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት። ለሕዝብ እና ለሀገር የሚቆረቆሩ ባለሀብት መኾናቸውንም ገልጸዋል። ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜም ኾነ በልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
ዛሬ ያዘጋጁት መርሐ ግብር ለወሎ ሕዝብ ምስጋና ለማቅረብ መኾኑን ነው የተናገሩት። የአካባቢው ሕዝብ አንድም ቀን ፕሮጄክቱ ሳይስተጓጎል እንዲጠናቀቅ ስላደረገ ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።
ፕሮጄክቱ ፋይዳው ብዙ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “አንድ ፕሮጄክት ሲጠናቀቅ ሌሎች መልካም ነገሮችን እንደሚሰብም” ተናግረዋል።
ወሎ በታሪክ፣ በሃይማኖት እና በተፈጥሮ የታደለ መኾኑን ነው የተናገሩት። ሐይቅ አካባቢ ደግሞ የብዙ ጸጋዎች ባለቤት መኾኑን አንስተዋል።
ሐይቅ እስጢፋኖስ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ እና የታሪክ ሃብታም መኾኑንም ጠቅሰዋል። የሐይቅ እስጢፋኖስ አባቶች መገለጫቸው ሥራ እና ጸሎት መኾኑንም አንስተዋል።
ፕሮጄክቱ ለአካባቢው የቱሪዝም መዳረሻነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት። እንዲህ አይነት ጸጋዎችን እያወጡ መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
