
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ፕሮጄክት ተጠናቅቆ መመረቁ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ሪዞርቱ ሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ባለቤት በላይነህ ክንዴ ቢኬጂ በኢትዮጵያ እያለማ ያለ ድርጅት ነው ብለዋል። ማኅበራዊ ኀላፊነቱንም እየተወጣ መኾኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ደግሞ በሁሉም አካባቢዎች እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥት በሰጣቸው ዕድል የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን መገንባታቸውን ተናግረዋል። ሪዞርቱ በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀው በትብብር ስለሠራን ነው፤ ሀገርን የሚያለማው ትብብር ነው ያሉት ባለሀብቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ በትብብር ልማቱ እንዲጠናቀቅ ማድረጉን ገልጸዋል።
ወደፊትም በትብብር መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሪዞርቱ የእናንተ ነው በደንብ ተጠቀሙበት፤ የተሰጠንን ዕድል በሚገባ እንጠቀመው ብለዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች የጫት ማሳቸውን መንጥረው በአትክልት እና ፍራፍሬ መሸፈናቸውንም ተናግረዋል። በትብብር ስለሠራን፣ ለበጎ ልማት በጋራ ስለቆምን፤ ሥራዬን ስለደገፋችሁ እና አብራችሁን ስለሠራችሁ አመሠግናችኋለሁ ነው ያሉት።
ሪዞርቱ የእናንተ ነው፤ ተጠቀሙበት፤ ሌሎች የልማት ሥራዎችንም በጋራ እንሠራለን ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ወሎ በታሪክ፣ በተፈጥሮ፣ በማኅበራዊ እና በሃይማኖታዊ ትስስር በወርቃማ እሴቶቹ የበለጸገ ሕዝብ ያለበት መኾኑን ተናግረዋል።
የሐይቅ ሪዞርት ለወሎ እና አካባቢው የቱሪዝም ልማት ከፍ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። ያለንን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን ከዘመናዊ ልማት ጋር በማስተሳሰር የማይናወጥ የኢኮኖሚ ግንባታ ምንጭ ኾኖ እንደሚያገለግልም ተናግረዋል።
የገበታ ለትውልድ ፕሮጄክት አካል የኾነው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት እንዲሠራ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በሐይቅ እንዲገነባ ሃሳብ ያመነጩትን፣ ያስጀመሩትን እና ያስፈጸሙትን አመሥግነዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
