
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን ሥራ አስጀምረዋል።
ይህንን አስመልክተውም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፦
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ጸጋን የመለየት፣ የማልማትና ወደ ሀብት የመቀየር ማሳያ እና የወሎ የብልጽግና ተስፋ ነው። ዛሬ በታሪካዊቷ የሐይቅ ከተማ ከማኅበረሰቡና ከአፋር ወንድሞቻችን ጋር በአንድነት ተገኝተን፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አነሣሽነት እና በ”ገበታ ለትውልድ” መርሐ ግብር የተገነባውን የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ሥራ ለማስጀመር በመቻላችን ታላቅ ደስታ ይሰማኛል።
ወሎ ማለት ኅብር ነው። ዛሬም በዚህ በዓል ላይ ከአፋር ወንድሞቻችን ጋር መገኘታችን ይህንኑ ውበታችንን የሚገልጥ ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከግንባታው ጅማሮ እስከ ፍጻሜው የ”መደመር” ዕሳቤ በተግባር የታየበት፣ የመንግሥት ሐሳብ፣ የባለ ሀብቱ ታታሪነት እና የሕዝቡ ትጋት የተሰባጠረበት ድንቅ ውጤት ነው። ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ሌት ተቀን ለጠበቁት የመከላከያ፣ የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት፣ እንዲሁም ለአካባቢው አመራርና ሕዝብ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።
ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ሪዞርቱን ውብ አድርገው ከመገንባት ባለፈ፣ ጫትን በምርጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያ በመተካት ለውጥ በተግባር እንደሚመጣ አሳይተዋል። ለሐይቅ ከተማ የገነቡት ትምህርት ቤትም ለትውልድ የሚተርፍ ተግባር ነው።
ዛሬ ያየነው ልማት የሰላም ውጤት ነው። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ሰላማቸውን አጥብቀው እንዲጠብቁ አደራ እላለሁ። በአንድነት እና በትጋት ከሠራን፣ ይህ ቀጣና የዕድገትና ብልጽግና መዳረሻ መሆኑ አይቀሬ ነው!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
