የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 57 በመቶ ሴቶችን ወደ መሪነት ማምጣት ተችሏል።

8
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚዎች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የአገልግሎት አሰጣጥ ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዲጂታል ሥርዓትን እንዲከተል እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአካል አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ ደንበኞች በዲጅታል ሥርዓት አገልግሎት እንዲያገኙ ተሠርቷልም ነው ያሉት።
በተቋሙ ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር 57 በመቶ መሪዎች ሴቶች ስለመኾናቸውም ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓትን እውቅና በመስጠት የሥልጠና እና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ ነውም ብለዋል። በባሕላዊ ዳኝነት ሥርዓቱ ሴቶች ተሳታፊ እንዲኾኑ ተሠርቷል ነው ያሉት። በዚህም በ12 ቀበሌዎች ሴቶች በባሕላዊ ዳኝነት ተሳታፊ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ኅብረት አቡሃይ ማኅበሩ የሴቶችን እና የሴት ሕጻናትን መብት ለማስከበር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በተለያዩ ተቋማት የሴቶችን ተጠቃሚነት እና መብት መጠበቅ ላይ ምልከታ እያደረጉ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።
በተከላካይ ጠበቆች አማካኝነት ነጻ የሕግ ድጋፍ እተየሰጠ ነው ያሉት ወይዘሮ ኅብረት ማኅበሩም ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሥራ ቦታውን በማዘመን፣ ዲጅታል አገልግሎትን በመተግበር እና የሕጻናት ማቆያ በማዘጋጀት ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር እየሠራ ያለው ተግባር አስደናቂ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleታዳሽ ኃይል በአርሶ አደሩ ቤት
Next article“የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ጸጋን የመለየት፣ የማልማትና ወደ ሀብት የመቀየር ማሳያ እና የወሎ የብልጽግና ተስፋ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ