ታዳሽ ኃይል በአርሶ አደሩ ቤት

20
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ የሚኾነው የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከውኃ፣ ከፀሐይ፣ ከነፋስ እና መሰል አማራጮች ነው የምታመነጨው።ይህም በተለይ ለገጠሩ ማኅበረሰብ በትናንሽ የኀይል ማመንጫዎች የኤሌክትሪክ ኀይልን ለማዳረስ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
🕯️ የገጠሩ ክፍል የኩራዝ ዘመን ሲታወስ
ቀደም ባሉት ዓመታት በምሽት ብርሃን ለማግኘት እንጨት ማቃጠል አልያም ነዳጅ በመጠቀም ኩራዝ ማብራት ግዴታ ነበር።
ይህም በተለይም የገጠሩን አካባቢ ነዋሪዎች ለጤና እና ለከፍተኛ ወጭ ይዳርጋቸው ነበር።
💡ታዳሽ ኃይል በክልሉ አርሶ አደሮች ቤት ከገባ በኋላስ?
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመጣው የፀሐይ ኀይል (የሶላር) ሥርዓት የገጠሩን ነዋሪዎች ሕይወት አቅልሏል።
አርሶ አደሮች ለጋዝ የሚያወጡትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ልጆች በምሽት እንዲያጠኑ እና በትምህርት ውጤታማ እንዲኾኑ እንዲሁም ከጭስ የጸዳ ከባቢን በመፍጠር የቤተሰብን ጤንነት ለመጠበቅ ማስቻሉን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች እና ቴክኖሎጅዎች ልማት ዳይሬክተር ታገለ አድማሱ ክልሉ ካሉት የተለያዩ የታዳሽ ኃይል አቅሞች እስካሁን በስፋት የተሠራባቸው የውኃ እና የፀሐይ ኀይል አማራጮች ናቸው ብለዋል።
ከዋናው የኀይል መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን በተለይ በሶላር ሥርዓት ተደራሽ ለማድረግ በሰፊው እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
👉 የአነስተኛ ሶላር ሥርዓቶች ሥርጭት
ባለፉት አምሥት ዓመታት በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ተደራሽ ላልኾኑ አርሶ አደሮች እስከ 12 ዋት አቅም ያላቸው አነስተኛ ሶላሮችን ለማዳረስ በተሠራው ተግባር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ኾነዋል።
በዚህ ዓመት 90 ሺህ ለማሰራጨት ታቅዶ 98 ሺህ የሶላር ሥርዓቶች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የአንድ ሌትር ኬሮሲን ዋጋ ከ100 ብር በላይ ኾኗል፤ አንድ አባውራ አርሶ አደር በዓመት 36 ሊትር ኬሮሲን እንደሚጠቀም ጠቅሰው ወደ ሶላር ሥርዓት በመሸጋገሩም ከዚህ ከፍተኛ ወጭ ሙሉ በሙሉ ነጻ መኾን ችሏል ብለዋል።
👉 በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ አነስተኛ የኀይል ማመንጫዎች ግንባታ
አቶ ታገለ የገጠሩን ማኅበረሰብ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ዋነኛ መፍትሔ የኾነውን አነስተኛ የኀይል ማመንጫዎች ግንባታ (mini grids) ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።31 የሚደርሱ የአነስተኛ የኀይል ምንጮች በጥናት ተለይተዋልም ነው ያሉት።
በክልሉ አቅም ሁለት አነስተኛ የኀይል ምንጮች በግንባታ ላይ መኾናቸውን እና ተጨማሪ አራት አነስተኛ ግሪዶችም በጨረታ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
👉 በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የሶላር ውኃ ፓምፖች ሥርጭት
አቶ ታገለ የገጠር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሶላር ሥርዓት ለመቀየር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። መስኖ በሶላር ማልማት እንዲችሉም አነስተኛ ፓምፖች እንደሚሠራጩ ገልጸዋል።
ታዳሽ ኀይል የገጠሩን ማኅበረሰብ ከጨለማ ወደ ብርሃን አሸጋግሮታል። ገጠሩን ከነዳጅ ነጻ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁ በመኾናቸው የግሉን ዘርፍ፣ የፕሮጀክቶችን እና የመንግሥትን ብርቱ ጥረት እንደሚጠይቅም ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫን መረቁ።
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 57 በመቶ ሴቶችን ወደ መሪነት ማምጣት ተችሏል።