ዲፕፌክ (Deepfake) ምንድን ነው?

5

 

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዲፕፌክ ማለት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በመጠቀም ትክክለኛ የሚመስሉ ግን ሀሰተኛ ምስሎችን፣ ድምጾችን እና ቪዲዮዎችን የመፍጠሪያ መንገድ ነው።

“ዲፕፌክ” የሚለው ስያሜ የመጣው Deep Learning (ጥልቅ ትምህርት) እና Fake (ሀሰተኛ) ከሚሉት ቃላት መኾኑን ከ”ፎርቲኔት ዶት ኮም” ድኅረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ቴክኖሎጂው የተለያዩ ሰዎችን ምስል እና ድምጽ በማቀናጀት እና በማጣመር፣ በገሃዱ ዓለም የሌሉ ሰዎችን ወይም ያልተከሰቱ ድርጊቶችን እውነተኛ አስመስሎ ይፈጥራል።

​ዲፕፌክ ለበጎ ተግባራት ሊውል ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን ለከፋ የዲጂታል ጥቃቶች መሣሪያነት እያገለገለ ይገኛል። ለዛሬው ዋና ዋናዎቹ አደገኛ አጠቃቀሞች እንካቹህ ብለናል።

​#ማጭበርበር እና የሀሰት ወሬዎች (Scams and Hoaxes)፦
ምስል እና ድምጽን በማቀናጀት ሰዎች ያልፈጸሙትን ወንጀል እንደፈጸሙ አስመስሎ የተቋማትን ስም ማጥፋት፣ በገበያ ዋጋቸው ላይ ውድቀት ማምጣት እና ገንዘብ መዝረፍን ዓላማ ያደረገ ነው።

#የታዋቂ ሰዎችን ዝና እና ክብር ለማውረድ፦ የታዋቂ ሰዎችን ምስል በማስመሰል ያልሠሩትን ሥራ እንደሠሩ ማስመሰል።

​#ምርጫን ማዛባት (Election Manipulation)፦የሀገር መሪዎች ያልተናገሩትን ንግግር በቪዲዮ በማቀናበር የሕዝብን አመለካከት መበከል እና በምርጫ ውጤት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር።

​#የማኅበራዊ ምሕንድስና ማጭበርበር (Social Engineering)፦
የቅርብ ሰዎችን ወይም የሥራ ኃላፊዎችን በማስመስል ገንዘብ እንዲላክ ወይም ሚስጥራዊ መረጃ እንዲሰጥ ማድረግ።

​#የተቀናጀ የሀሰት መረጃ ጥቃት (Automated Disinformation attacks )፦የተለያዩ የሴራ ትንተናዎችን እና የተሳሳቱ ማኅበራዊ መረጃዎችን በስፋት በማሠራጨት ማኅበረሰቡን ግራ ማጋባት።

​#የማንነት ሥርቆት እና የፋይናንስ ወንጀል፦የሰዎችን ድምጽ እና ምስል በመጠቀም የሀሰት ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ በሰዎች ሥም የባንክ አካውንት መክፈት እና ግብይቶችን መፈጸም ነው። ይህም የሳይበር ወንጀልን እጅግ አደገኛ እያደረገው እንደኾነም ይነገራል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በ2018 በጀት ዓመት 15 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲያወጡ እየተሠራ ነው።
Next article🇪🇹”በባንዲራው አምላክ ሰላማችን ይከበር” የቢቸና እና የእነማይ ነዋሪዎች