
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ዕኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያደርግ ትልቅ መድረክ ነው።
ወይዘሮ ስለናት ካሳሁን የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ካርድ ቀድመው በማውጣት በእጃቸው አድርገዋል።
“ይወክለኛል የምለውን ፓርቲ በድምጼ ለመወሰን ያስችለኛል፤ የምንለብሰውን ልብስ በብራችን መርጠን እንደምንገዛው የሚያሥተዳድረንን ፓርቲም በካርዳችን እንመርጣለን” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር እንዬ ገነቱ ፌዴሬሽኑ በክልሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሴቶችን በአደረጃጀት አቅፎ ይዟል ብለዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመራጭነት እና በታዛቢነት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሥራዎች ሲተገበሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
ሴቶች መብታቸውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን ፓርቲ መምረጥ የሚችሉት የምርጫ ካርድ በእጃቸው ሲያደርጉ ብቻ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም በአደረጃጀት ለሴቶች ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። በርካታ ሴቶችም የምርጫ ካርድ በእጃቸው እያደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
3ሺህ 500 የሚኾኑ ሴቶችን በታዛቢነት እንዲሳተፉ የመለየት ሥራ እንደተከናወነም ገልጸዋል።
የፌዴሬሽኑ አባላት በታዛቢነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለ53 አሥተባባሪ ሴቶች ሥልጠና መስጠት መጀመሩንም አንስተዋል።
ምረጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
