መረጃን ከመቀበል በፊት ለምን? በማን? እንዴት’ን? ማስቀደም!

11
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚዲያ ንቃት (media literacy) ማለት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ እና በሌሎች የዲጂታል አማራጮች የሚተላለፉ መልዕክቶችን የመረዳት፣ የመተንተን እና የመገምገም ክህሎት ነው።
ይህ ክህሎት መረጃን ከመቀበል በፊት “ለምን? በማን? እንዴት?…” ብሎ የመጠየቅ ልምድን ያዳብራል።
የሚዲያ ንቃት አንድ ግለሰብ የሚያገኘውን መረጃ ትክክለኛነት፣ እውነት ወይም ሐሰትን የሚለይበት እንዲኹም መረጃውን በንቃት የሚመረምርበት ክህሎት ነው።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር አበራ የኔወርቅ (ዶ.ር) ቀደም ባሉት ጊዜያት መረጃዎች በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በጋዜጣ ብቻ የተገደቡ እንደነበሩ አንስተዋል።
ነገር ግን በአኹኑ የዲጂታል ዘመን ማንኛውም ግለሰብ መረጃ ማሠራጨት የሚችልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል። ስለዚህ መረጃን የማጣራት ክህሎት የግድ መኾኑን አንስተዋል።
ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ በመሳሰሉ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ መረጃዎችን እንዳለ የመቀበል እና የማሠራጨት ልምድ በመስፋፋቱ ሐሰተኛ መረጃዎች “እንደ ሰደድ እሳት” የመዛመት እድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቁ መረጃዎችን የማጣሪያ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ገልጸዋል።
ጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ ወይንም ጎግል ሌንስ የመሳሰሉ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም አንድ ፎቶ ከዚህ ቀደም የተለቀቀ መኾን አለመኾኑን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስም (AI) የሰዎችን ድምጽ እና እንቅስቃሴ አስመስለው የሚሠሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማጣራት የሚያስችል ማጣሪያ ሶፍትዌሮች እንዳሉት ገልጸዋል።
የበለጸጉት ሀገራት የሚዲያ ንቃት ትምህርት በመስጠት ጠንካራ የመረጃ ማጣሪያ ተቋማት እንዳሏቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የመረጃ ማጣራት ልምድን ግን ደካማ ብለውታል።
ውስንነቱም በተራው ማኅበረሰብ ዘንድ ብቻ ሳይኾን በሚዲያ እና በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጭምር የሚታይ መኾኑ አሳሳቢ ነው ባይ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ለነጻነት እታገላለሁ የሚል ኃይል እንዴት ንጹሐንን እያገተ ገንዘብ ይዘርፋል?”
Next articleበጎንጅ ቆለላ ወረዳ የመራጮች ምዝገባ በንቃት እየተካሄደ ነው።