
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በማኅበረሰቡ ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተለ ነው። የሰዎችን ሕይወትም እያጎሳቆለ ይገኛል።
በጫካ ያሉት ኃይሎች ባደረሱት ጥፋት ሕዝብ ለሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሣራ እየተጋለጠ መሆኑን በየአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልጠቀስናቸውና በጫካ ባሉ ኃይሎች የግፍ ሰለባ የኾኑት
የእነብሴ ሳርምድር ወረዳ ነዋሪው እንዳሉት ከቀያቸው ታፍነው ለአምስት ሰዓታት በፈጀ የእግር ጉዞ ወደ ጫካ ተወስደዋል።
300 ሺህ ብር ካላመጣህ እንገድልሃለን የሚል ዛቻ እና ስቃይም አድርሰውባቸዋል።
በኋላም የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ተሠማርቶ የሕግ ማስከበር ተግባር ሢሠራ ግለሰቡም የራሳቸውን ስልት ተጠቅመው ከታጣቂዎች አምልጠዋል።
በጫካ ያሉ ኃይሎች መሪዎች ዓላማቸው በዝርፊያ ሃብት ማከማቸት ላይ መኾኑንም ባለታሪኩ አንስተዋል። የድሃን ልጅ ለጦርነት እየማገዱ እንደኾነ ማረጋገጣቸውን ነው የገለጹት። “ለነጻነት እታገላለሁ የሚል ኃይል እንዴት ንጹሐንን እያገተ ገንዘብ ይዘርፋል?” ሲሉም በምሬት ተናግረዋል።
ሰሞኑን የሰላም አማራጭ ተቀብለው የገቡት ፍቅሩ ሙሉዬ እና አየነው አስፋው ይህንኑ እውነት ሲያረጋግጡ ተደምጠዋል። በጫካ ያሉት ኃይሎች ለእውነተኛ ትግል ሳይኾን ሃብት ሥብሠባ ላይ ናቸው ነው ያሉት።
በተለይም ፍቅሩ ሙሉዬ እንደተናገረው ግለሰብ እየታፈነ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እየተጠየቀ እና እንዲከፍል እየተገደደ ትግሉ መነገጃ መኾኑን አጋልጧል።
የቡድኑ መሪዎች ዘመናዊ ስልክ ይዘው ጫካ ለጫካ ይሹለከለካሉ እንጂ ቆመው አይዋጉም፤ እንዲዋጋ የሚገደደው የድሃ ልጅ ነው የሚለው ደግሞ የቀድሞ ታጣቂ አመራር የነበረው አየነው አስፋው ነው።
በጫካ ያሉ ኃይሎች መሪዎች በጥቅም የታወሩ፣ ሕዝቡን እያታለሉ የፖለቲካ ሸፍጥ እየፈጸሙ ነው ብሏል። ከውጭ ኃይሎች ጋር የባንዳነት ጋብቻ በመፈጸም በተራዘመ ግጭት የግላቸውን ኢኮኖሚ እያካበቱ ኪሳቸውን እያደለቡ ነው በማለት ያጋልጣሉ።
እኛ ችግሩን ተገንዝበን ለሕዝባችን ሰላም ለመስጠት መጥተናል፤ በቀጣይም ቀሪ በጫካ የሚገኙ ጓደኞቻቸው የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመቀበል መግባት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
