ኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ሥርዓቷን ለመገንባት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን ፈሰስ አድርጋለች።

8
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በጋራ ያዘጋጁት ብሔራዊ የግብርና ምርምር ሥርዓት መድረክ እየተካሄደ ነው። “ሀገራዊ የግብርና ምርምር ሥርዓት ለኢትዮጵያ ተቋማዊ እና ስትራቴጂካዊ ቅንጅት እንዲሁም ለለውጥ ጉዞ” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በውይይት መድረኩ ከ1940ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ሥርዓት ዕድገትን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍም ቀርቧል።
የግብርና ሚኒስትር ድኤታ መለሰ መኮንን (ዶ.ር) የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በመኾን የብሔራዊ ልማት አጀንዳ ምሰሶ የኾነውን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ ባለፉት አስርት ዓመታት እንደሀገር የምርምር ሥርዓቱን በማስፋት እና በመገንባት ረገድ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ተደርጓል ብለዋል። ይህም በዘርፉ ቴክኖሎጂ፣ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች፣ የሰው ኀይል አቅምን በማጓልበት እና በምርታማነት ዕድገት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ የታለመውን ግብ ለማሳካት ተቋማት በሙሉ አቅም በቅንጅት መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል። የመጨረሻው ግብ መኾን ያለበት አግባብነት ያለው ዕውቀት የሚያመነጭ፣ ፈጠራን የሚደግፍ፣ የአርሶአደሮችን ሕይወት የሚያሻሽል እና አይበገሬ የምግብ አቅምን የሚያጎለብት የምርምር ሥርዓት መገንባት ነው ብለዋል ሚኒስትር ድኤታው።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ.ር) ኢንስቲትዩቱ በግብርናው ሥነ ምህዳር ዙሪያ ያለውን ትስስር ለማጠናከር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። መድረኩ የምርምር አቅምን በማጎልበት በሳይንስ፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር ዓላማ ያደረገ እንደኾነም አስረድተዋል።
የምርምር ተቋማት የተበታተነ የግብርና ምርምርን ወደ አንድ ማዕቀፍ በማምጣት ሦሥቱ የምርምር ተቋማት ወጭ ቆጣቢ እና ቅንጅታዊ አሠራርን በውጤታማነት እንዲተገብሩ አጋዥ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጠንካራ የግብርና ምርምር ሥርዓትን መገንባት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነትም ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ የከፍተኛ የትምህርት የምርምር ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላምን እያረጋገጡ አስፈላጊውን ገቢ መሠብሠብ እና ልማትን መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መከሩ።